የሐዋርያት ሥራ 24
24
ስለ ከሳሾች መምጣት
1በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት። 2ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ 3“ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስትመሰገን አግኝተናታል። 4ነገር ግን ነገር እንዳላበዛብህ በአጭሩ ትሰማኝ ዘንድ#ግሪኩ “በቸርነትህ” የሚል ይጨምራል። እለምንሃለሁ። 5ይህን ሰው ሲሳደብና ወንጀል ሲሠራ፥ አይሁድንም ሁሉ በየሀገሩ ሲያውክ፥ ናዝራውያን የተባሉት ወገኖች የሚያስተምሩትንም ክህደት ሲያስተምር#ግሪኩ “የመናፍቃን፥ የናዝራውያን መሪ ሆኖ አግኝተነዋል” ይላል። አግኝተነዋል። 6ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም ልንፈርድበት ፈልገን ነበር። 7ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ጭንቅ ከእጃችን ነጥቆ ወደ አንተ ላከው። 8ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዛቸው፤ የከሰስንበትንም ነገር ሁሉ መርምረህ ከእርሱ ልትረዳ ትችላለህ።” 9አይሁድም፥ “እውነት ነው፤ እንዲሁ ነው” ብለው መለሱ።
የጳውሎስ መልእክት
10ሀገረ ገዢውም እንዲናገር ጳውሎስን ጠቀሰው፤ ጳውሎስም እንዲህ አለ፥ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ አስተዳዳሪ እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ጠባያቸውንም ታውቃለህ። አሁንም ደስ እያለኝ ክርክሬን አቀርባለሁ። 11እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይሆን ልታውቀው ትችላለህ፤ 12በምኵራብ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ቢሆን፥ በከተማም ቢሆን ሕዝብን ሳውክ፥ ከማንም ጋር ስከራከር አላገኙኝም። 13በሚከስሱኝ ሁሉ በፊትህ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። 14ነገር ግን ይህን አረጋግጥልሃለሁ፤ እኔ በሕግ ያለውን፥ በነቢያትም የተጻፈውን ሁሉ አምኜ እነርሱ ክህደት ብለው በሚጠሩት ትምህርት የአባቶችን አምላክ አመልከዋለሁ። 15እነርሱም ለጻድቃንና ለኃጥኣን የሙታን ትንሣኤ ይሆን ዘንድ እንደሚጠብቁ ለእኔም እንዲሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ አለኝ። 16እንዲሁ እኔም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ የማታወላውል ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እጋደላለሁ። 17ከብዙ ዓመታትም በኋላ ለወገኖች ምጽዋትንና መሥዋዕትን ላደርግ መጣሁ። 18#የሐዋ. 21፥17-28። በዚያም ጊዜ ከእስያ የመጡ አይሁድ ከሕዝብ ጋር በመከራከር፥ ወይም በፍጅት ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። 19አሁንም በእኔ ላይ ነገር ከአላቸው ወደ አንተ ይምጡና ይክሰሱኝ። 20ወይም እኔ በሸንጎ ቆሜ ሳለሁ ያገኙብኝ በደል እንደ አለ እነዚህ ራሳቸው ይመስክሩ። 21#የሐዋ. 23፥6። በመካከላቸው ቆሜ ከአስተማርኋት አንዲት ትምህርት በቀር ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም። ‘ሙታን ይነሣሉ’ በማለቴም ዛሬ በአንተ ዘንድ በእኔ ይፈረድብኛል።”
22ፊልክስ ግን አይሁድ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያንን ወገኖች ሕግና ትምህርት እንደሚቃወሙ ያውቅ ነበር፤#ግሪኩ “ፊልክስ ግን የትምህርቱን ነገር አጥብቆ ዐውቆአልና” ይላል። ስለዚህም “እንኪያስ የሺ አለቃው ሉስዮስ በመጣ ጊዜ ነገራችሁን እናውቅ ዘንድ እንመረምራለን” ብሎ ቀጠራቸው። 23የመቶ አለቃውንም ጳውሎስን እንዲጠብቀው፥ በሰፊ ቦታም እንዲያኖረው፥ እንዳያጠብበትም፥ ሊያገለግሉት በመጡ ጊዜም ከወዳጆቹ አንዱን ስንኳ እንዳይከለክልበት አዘዘ።
24ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ ከአይሁዳዊት ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ። ልኮም ጳውሎስን አስጠራው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመንም የሚናገረውን ነገር ሰማው። 25እርሱም ስለ ጽድቅና ስለ ንጽሕና፥ ስለሚመጣውም ኵነኔ በነገራቸው ጊዜ በዚህ የተነሣ ፊልክስ ፈራና ጳውሎስን፥ “አሁንስ ሂድ፤ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ” አለው። 26ፊልክስም እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ የሚሰጠው መስሎት ነበር፤ ስለዚህ ዘወትር ይጠራውና ያነጋግረው ነበር። 27ሁለት ዓመትም ካለፈ በኋላ፥ ፊልክስ ተሻረና ጶርቅዮስ ፊስጦስ የሚባል ሌላ ሀገረ ገዢ በእርሱ ቦታ መጣ፤ ፊልክስም በግልጥ ለአይሁድ ሊያዳላ ወደደ፤ ስለዚህም ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 24: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in