ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2:6-15
ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2:6-15 አማ2000
እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ። በእርሱ ተመሥርታችሁ ታነጹ፤ በምስጋናው ትበዙ ዘንድ፥ በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ። ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል። እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ። ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው። አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው።