ኦሪት ዘዳግም 15
15
ዕዳ የሚሠረዝበት ዓመት
(ዘሌ. 25፥1-7)
1“በየሰባቱ ዓመት የዕዳ ምሕረትን ታደርጋለህ። 2ለምሕረቱም የሚገባ ትእዛዝ ይህ ነው፤ ባልንጀራህ ወይም ወንድምህ የሚከፍልህን ገንዘብ ሁሉ አትከፈል፤ የአምላክህ የእግዚአብሔር ምሕረት ተብላለችና። 3ከባዕድ ግን በእርሱ ዘንድ ያለህን ሁሉ መቀበል ትችላለህ፤ በወንድምህ ላይ ያለውን ሁሉ ግን ተውለት። 4አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ አምላክህ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይባርክሃልና በመካከልህ ድሃ አይኖርም፤ 5አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ 6አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ብዙ ታበድራለህ፤ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፤ አንተን ግን አይገዙህም።
7“አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ካሉ ከተሞች በአንዲትዋ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢቸገር ልብህን አታጽና፤ ለወንድምህ ከመስጠት እጅህን አትመልስ። 8ነገር ግን እጅህን ለእርሱ ዘርጋ፤ የለመነህንም ሁሉ ስጠው።#ዕብ. “አበድረው” ይላል። 9ሰባተኛው ዓመት የምሕረት ዓመት ቅርብ ነው፤ አልሰጠውምም ብለህ ክፉ ዐሳብ በልብህ እንዳታስብ ለራስህ ዕወቅ። ወንድምህም ዐይኑን በአንተ ላይ ያከፋል፤ እርሱም ወደ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ይጮሃል፤ ኀጢአትም ይሆንብሃል። 10እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና ፈጽመህ ስጠው፤ የለመነህንም ያህል አበድረው፤ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት። 11ድሃ ከምድርህ ላይ አይታጣምና ስለዚህ እኔ፦ በሀገርህ ውስጥ ላለው ድሃ፥ ለሚለምንህም ወንድምህ እጅህን ዘርጋ ብዬ አዝዝሃለሁ።
ባሮች ነጻ የሚወጡበት ዓመት
(ዘፀ. 21፥1-11)
12“አንተም ወንድምህን ዕብራዊዉን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፤ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጥተህ ልቀቀው። 13ከአንተም ዘንድ አርነት አውጥተህ በለቀቅኸው ጊዜ ባዶውን አትልቀቀው። 14ነገር ግን ከበጎችህ፥ ከእህልህም፥ ከወይንህም መጭመቂያ ስንቅ ትሰንቅለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። 15አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ ዐስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። 16እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለ ወደደ፥ በአንተም ዘንድ መኖር መልካም ስለሆነለት፦ ‘አልወጣም’ ቢል፥ 17አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን#ግእዙ “አፍንጫውን” ይላል። ትበሳዋለህ፤ ለዘለዓለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህም ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ። 18እርሱንም አርነት ባወጣኸው ጊዜ የምንደኝነቱን ሥራ ሁለት ዕጥፍ አድርጎ ስድስት ዓመት አገልግሎሃልና አያስጨንቅህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል።
የእንስሳት በኵራት
19“ላምህና በግህ የወለዱትን ተባት የሆነውን በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትቀድሳለህ፤ በበሬህ በኵራት አትሥራበት፤ የበግህንም በኵራት አትሸልት። 20አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላው። 21ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፥ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው፥ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው። 22በሀገርህ ውስጥ ትበላዋለህ፤ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ፥ ሚዳቋንና ዋሊያን እንደሚበሉ ይበሉታል። 23ነገር ግን ደሙን በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 15: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in