ኦሪት ዘዳግም 31
31
ኢያሱ በሙሴ ፋንታ እንደ ተተካ
1ሙሴም ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናግሮ ጨረሰ። 2አላቸውም፥ “እኔ ዛሬ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም፦ ‘ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል። 3አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሄዳል። 4እግዚአብሔር አምላክም ባጠፋቸው በዮርዳኖስ ማዶ በሚኖሩ በሁለቱ በአሞሬዎናውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ፥ በምድራቸውም እንዳደረገ እንዲሁ ያደርግባቸዋል። 5እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፤ እንዳዘዝኋችሁም ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ። 6ጽና፤ በርታ፤ አትፍራ፤ ከፊታቸውም አትደንግጥ፤ አትድከም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፤ አይተውህምም። 7ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት፦ ‘አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፤ በርታ። 8በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አይጥልህም፤ አይተውህም፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ’ ” አለው።
ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንደሚገባው
9ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፤ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ፥ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት። 10ሙሴም በዚያች ቀን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ በምሕረት ዓመት በዳስ በዓል፥ 11እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ቦታ በአንድነት በሚሄድበት ጊዜ፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው። 12ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ሰምተው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችና ሴቶችን፥ ሕፃኖቻችሁንም፥ በሀገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ። 13የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።”
ሙሴና ኢያሱ ከእግዚአብሔር መመሪያ መቀበላቸው
14እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የምትሞትበት ቀን እነሆ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም” አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ቆሙ። 15እግዚአብሔርም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በደመና ዐምድ ወረደ፤ የደመናውም ዐምድ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ላይ ቆመ። 16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ታንቀላፋለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፤ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፤ እኔንም ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ። 17በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፤ እተዋቸውማለሁ፤ ፊቴንም ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን፦ በእውነት አምላካችን እግዚአብሔር ትቶናልና፥ በእኛም መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። 18ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ። 19አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፤ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት። 20ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም፥ ከጠገቡም በኋላ ይስታሉ፤ ሌሎችን አማልክትም ወደ ማምለክ ይመለሳሉ፤ እኔንም ያስቈጡኛል፤ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። 21ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው ክፋታቸውን አውቃለሁና፥ ከአፋቸውና ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትቆማለች።”#ዕብ. “ትመሰክራለች” ይላል። 22ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፤ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት። 23የነዌንም ልጅ ኢያሱን፥ “የእስራኤልን ልጆች እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ወደ ማለላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፤ በርታ፤ እርሱም ከአንተ #ዕብ. ምዕ. 31 ቍ. 23 እግዚአብሔርን ባለቤት አድርጎ በአንደኛ መደብ ይጽፋል። ጋር ይሆናል” ብሎ አዘዘው።
24እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች እስከ መጨረሻ በመጽሐፍ ጽፎ ከፈጸመ በኋላ፥ 25የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 26“ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት። 27እኔ ዐመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? 28ይህን ቃል በጆሮአቸው እነግር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን አለቆች፥ ሽማግሌዎቻችሁን ሁሉ፥ ሹሞቻችሁንም፥ ጻፎቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤ 29ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ፥ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል።”
የሙሴ መዝሙር
30ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህችን መዝሙር ቃሎች እስከ መጨረሻው ድረስ ተናገረ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 31: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in