መጽሐፈ ምሳሌ 10
10
ልዩ ልዩ የሰሎሞን ምሳሌዎች
1ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤
ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናታል።
2የሀብት ድልብ ለኃጥኣን አይጠቅምም፤#ዕብ. “በኃጢአት የተገኘ ገንዘብ አይጠቅምም” ይላል።
ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች።
3እግዚአብሔር ጻድቅት ነፍስን አያስርብም፤
የኃጥኣንን ሕይወት ግን ከምድር ያስወግዳል።
4የሐኬተኛ እጅ ችግረኛ ያደርጋል፤
የትጉህ እጅ ግን ባለጠጋ ያደርጋል።
5የተማረ ልጅ ብልህ ይሆናል።
ሰነፍ ልጅ ግን ራሱን ተገዥ ያደርጋል።
ብልህ ልጅ ከቃጠሎ ይድናል፤
ኀጢአተኛ ልጅ ግን በአውድማ ነፋስ የሚጨብጥ ይሆናል።#የመጀመሪያዎቹ 4 መስመሮች በዕብራይስጥ የሉም።
ብልህ ልጅ በመከር ጊዜ ይሠራል።
ሰነፍ ልጅ ግን በመከር ጊዜ ይተኛል።
6የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው።
የኃጥኣንን አፍ ግን ኀዘን በድንገት ይዘጋዋል።
7የጻድቃን መታሰቢያ ከምስጋና ጋር ነው።
የኃጥኣን ስም ግን ይጠፋል።
8በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤
በከንፈሩ የማይታገሥ ግን በመሰናክል ይወድቃል።
9በየውሃት የሚሄድ ተማምኖ ይኖራል፤
መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል።
10ለክፋት በዐይኑ የሚጠቃቀስ ለሰው ኀዘንን ይሰበስባል፥
በግልጽ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል።
11የሕይወት ምንጭ በጻድቃን አፍ ነው፥
የኃጥኣንን አፍ ግን ጥፋት ይከድነዋል።
12ቍጣ ጥልን ያነሣሣል።
ፍቅር ግን የማይጣሉትን ሁሉ ይሸፍናቸዋል።
13ብልህ ሰው ከከንፈሩ ጥበብን ያወጣል፤
አእምሮ የጐደለውንም ሰው በበትር ይመታል።
14ጠቢብ ዕውቀትን ይሸሽጋል፤
የችኩል አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል።
15የባለጠጋ ሀብት የጸናች ከተማ ናት፤
የዕውቀት ድህነት ግን የኀጢአተኞች ጥፋት ነው።
16የጻድቃን ሥራ ሕይወትን ያደርጋል፤
የኃጥኣን ፍሬ ግን ኀጢአት ነው።
17ተግሣጽ የሕይወትን መንገድ ይጠብቃታል፤
በተግሣጽ የማይዘለፍ ግን ይስታል።
18ልዝብ ከንፈሮች ጥልን ይሸፍናሉ፤
ስድብን የሚያወጡ ግን ሰነፎች ናቸው።
19ኃጥእ ከነገር ብዛት የተነሣ ከኀጢአት አያመልጥም፤
ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።
20የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤
የኃጥኣን ልብ ግን ይጐድላል።
21የጻድቃን ከንፈሮች የሩቁን ያውቃሉ፤
ሰነፎች ግን በድህነት ይሞታሉ።
22የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ሆና ባለጠጋ ታደርጋለች፥
ኀዘንንም ወደ ልብ አታመጣም።
23ሰነፍ ሰው በመሳቁ ክፉን ይሠራል፤
ጥበብ ግን ለሰው ዕውቀትን ትወልዳለች።
24ኃጥእ ወደ ጥፋት ይመለሳል፥
የጻድቅ ምኞቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች ናት።
25ኃጥእ እንደ ዐውሎ ነፋስ ኅልፈት ይጠፋል፤
ጻድቅ ግን ተሰውሮ ለዘለዓለም ይድናል።
26ጨርቋ ለጥርስ፥ ጢስም ለዐይን ጎጂ እንደ ሆነ፥
ኀጢአትም ለሚሠሯት እንዲሁ ናት።
27እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ያረዝማል፤
የኃጥኣን ዕድሜ ግን ያጥራል።
28ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች፤
የኃጥኣን ተስፋ ግን ትጠፋለች።
29እግዚአብሔርን መፍራት ለደግ ሰው ብርታት ነው፥
ጥፋት ግን ክፋት ለሚያደርጉ ነው።
30ጻድቃን ለዘለዓለም አይናወጡም፤
ኃጥኣን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም።
31የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤
የዐመፀኛ ምላስ ግን ይጠፋል።
32የጻድቃን ከንፈሮች ሞገስን ያፈስሳሉ፤
የኃጥኣን አፍ ግን ከዕውቀት ይከለከላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 10: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in