YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 15

15
1ቍጣ ጥበበኞችን ታጠፋለች፤
የለዘበ ቃል ቍጣን ይመልሳል፥
ሻካራ ቃል ግን ጠብን ያነሣሣል።
2የጠቢባን ምላስ መልካም ነገርን ታውቃለች፤
የአላዋቂዎች አፍ ግን ክፋትን ይናገራል።
3የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉ ቦታ ናቸው፤
ክፉዎችንና ደጎችንም ይመለከታሉ።
4ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤
የሚጠብቀው ግን የዕውቀት መንፈስን ይሞላል።
5አላዋቂ ልጅ የአባቱን ተግሥጽ ያቃልላል፤
ተግሣጽን የሚጠብቅ ግን ዐዋቂ ነው።
እውነት ከበዛ ዘንድ ብዙ ኀይል አለ፥
ኀጢአተኞች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፥
6በጻድቃን ቤቶች ብዙ ኀይል አለ፥
የኀጢአተኞች ፍሬ ግን ይጠፋል።
7የጠቢባን ከንፈሮች በዕውቀት የታሰሩ ናቸው፤
የሰነፎች ልብ ግን የጸና አይደለም።
8የክፉዎች መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤
የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።
9የክፉዎች መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤
ጽድቅን የሚከተሉትን ግን እግዚአብሔር ይወድዳቸዋል።
10የቅኖች ትምህርት በሚያልፉ ሰዎች ትታወቃለች።
ተግሣጽን የሚጠሉ ግን በውርደት ይሞታሉ።
11ሲኦልና ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቁ ናቸው፤
የሰዎች ልብማ እንዴት የታወቀ አይሆን?
12አላዋቂ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥
ከጠቢባንም ጋር አይነጋገርም።
13ልብ ደስ ሲለው ፊት ይበራል፤
ልብ ሲያዝን ግን ፊት ይጠቍራል።
14ቀና ልብ ዕውቀትን ትፈልጋለች።
የአላዋቂዎች አፍ ግን ክፋትን ይናገራል።
15የክፉዎች ዐይኖች ሁልጊዜ ክፋትን ይመለከታሉ፤
ደጋግ ሰዎች ግን ሁልጊዜ ዝም ይላሉ።
16እግዚአብሔርን በመፍራት የሚገኝ ጥቂት ሀብት
እግዚአብሔርን ባለመፍራት ከሚገኝ ብዙ መዝገብ ይሻላል።
17ጥል ካለበት የሰባ ፊሪዳ፥
ደስታና ፍቅር ያለበት የጎመን ወጥ ይሻላል።
18ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤
ትዕግሥተኛ ሰው ግን የሆነውን ስንኳ ያጠፋል።
ትዕግሥተኛ ሰው ክርክርን ያጠፋል፥
ኀጢአተኛ ሰው ግን ጠብን ፈጽሞ ያነሣል።
19የሰነፎች መንገዶች እሾህ የተከሰከሰባቸው ናቸው፥
የጽኑዓን መንገዶች ግን ጥርጊያ ናቸው።
20ብልህ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤
አላዋቂ ልጅ ግን እናቱን ያሰድባል።
21የአላዋቂ ሰው መንገዶች ጠማሞች ናቸው፤
ብልህ ሰው ግን አቅንቶ ይሄዳል።
22ማኅበርን የሚያከብሩ ማስተዋልን ገንዘብ ያደርጋሉ።
ምክርም በመካሮች ልብ ትኖራለች።
23ክፉ ሰው ግን ምክርን አይሰማትም፤
ለማኅበሩም መልካምና መጥፎ ነው የሚለው የለም።
24ሸሽቶ ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ፥
የአስተዋይ ሰው ልብ የሕይወት መንገድ ነው።
25እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት ያፈርሳል፤
የመበለቷን ወሰን ግን ያጸናል።
26ዐመፃን ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ የተናቀ ነው፤
የንጹሓን ቃል ግን ያማረ ነው።
27መማለጃን የሚቀበል ራሱን ያጠፋል፤
መማለጃ መቀበልን የሚጠላ ግን ይድናል።
በምጽዋትና በእምነት ኀጢአት ይሰረያል።
እግዚአብሔርንም በመፍራት ክፉ ሁሉ ይወገዳል።
28የጻድቃን ልብ ታማኝነትን ይማራል፤
የኃአጥኣን አፍ ግን ክፋትን ይመልሳል።
የደጋግ ሰዎች መንገዶች በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱ ናቸው፥
ስለ እነርሱም ጠላቶች ወዳጆችን ይሆናሉ።
29እግዚአብሔር ከኃጥኣን ፈጽሞ ይርቃል፤
የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።
ከዐመፃ ጋር ካለ ብዙ ሀብት ይልቅ፥
ከእውነት ጋር ያለ ጥቂት ሀብት ይሻላል።
አካሄዱ ከእግዚአብሔር ይቃናለት ዘንድ፥
የደግ ሰው ልብ እውነትን ያስባል።
30መልካምን ነገር የሚያይ ዐይን ልብን ደስ ያሰኛል፥
መልካም ዜናም አጥንትን ያለመልማል።
31የብልህን ተግሣጽ የሚሰማ ሰው
ከጠቢባን ጋራ አንድ ይሆናል።
32ከተግሣጽ የሚከላከል ራሱን ይጠላል።
ተግሣጽን የሚወድድ ግን ራሱን ይወድዳል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in