YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 16

16
1እግዚአብሔርን መፍራት በጎ ዕውቀትና ጥበብ ነው።
ለሚመልስላትም የክብር መጀመሪያ ናት፥
የዋሃንንም ክብር ትከተላቸዋለች።#“የዋሃንንም ክብር ትከተላቸዋለች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
2የትሑት ሰው ሥራ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው፥
3ኃጥኣን ግን በክፉ ቀን ይጠፋሉ።
4በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው።
በዐመፃ እጅን በእጅ የሚመታ አይነጻም።
5የደግ መንገድ መጀመሪያ እውነት መሥራት ነው፥
እርሱም መሥዋዕትን ከመሠዋት ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነው።
6እግዚአብሔርን የሚፈልግ ዕውቀትን ከጽድቅ ጋር ያገኛል፥
7ቅንነትን የሚሹ ሰላምን ያገኛሉ።
8የእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ከእውነት ጋር ነው።
9ኃጥእ ለክፉ ቀን ይጠበቃል።
10ጥበብ በንጉሥ አፍ አለ፥
አፉም በፍርድ አይሳሳትም።
11የእግዚአብሔር ፍርድ እንደ ሚዛን ውልብልቢት ነው፤
ሥራውም የከረጢት ደንጊያ ነው።
12ክፉን የሚሠራም በንጉሥ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
የፍርድ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና።
13የእውነት ከንፈር በንጉሥ ዘንድ የተወደደ ነው፥
ቅን ነገርንም ይወድዳል።
14የንጉሥ ቍጣ እንደ መልአከ ሞት ነው፤
ብልህ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
15የንጉሥ ልጅ እንደ ሕይወት ብርሃን ነው፥
በማያስደስቱትም ዘንድ የማታ ደመና ነው።
16ጥበብን ገንዘብ ማድረግ ከወርቅ ይመረጣል።
ዕውቀትንም ገንዘብ ማድረግ ከብር ይሻላል።
17የሕይወት መንገዶች ከክፉ ያርቃሉ፤
የጽድቅ ጎዳና የዘመን ብዛት ነው።
ትምህርትን የሚቀበል በበጎ ይኖራል።
ተግሣጽን የሚጠብቅም ብልሃተኛ ይሆናል።
መንገዶቹን የሚጠብቅ ሰውነቱን ይጠብቃል፥
ሕይወትንም የሚወድድ አፉን ይጠብቃል።
18ከጥል በፊት ስድብ ይቀድማል፥
ከመውደቅም በፊት ክፋትን ማወቅ።
19ከተሳዳቢዎች ጋር ምርኮን ከሚካፈል፥
በትሕትና ቍጣን የሚያርቅ ይሻላል።
20በሥራ ዐዋቂ የሆነ መልካም ነገርን ያገኛል፤
በእግዚአብሔርም የታመነ ብፁዕ ነው።
21ጠቢብን ሰዎች ዐዋቂ ይሉታል፥
ነገሩም ጣፋጭ የሆነውን እጅግ ያደምጡታል።
22በጎ ዐሳብ ገንዘብ ላደረጋት ሰው የሕይወት ምንጭ ናት፤
የሰነፎች ትምህርት ግን ክፉ ናት።
23የጠቢብ ልብ ከአፉ ይታወቃል፥
በከንፈሩም ዕውቀትን ይለብሳል።
24ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤
ጣፋጭነቱም የነፍስ መድኀኒት ነው።
25ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤
ፍጻሜዋ ግን የሲኦል ጕድጓዶችን ይመለከታል።
26ሰው በድካሙ ለራሱ ይደክማል፥
ከራሱም ጥፋትን ያርቃል።
ጠማማ ግን በአፉ ጥፋትን ይለብሳል።
27አላዋቂ ሰው ለራሱ ክፋትን ይምሳል፥
በከንፈሩም እሳትን ይሰበስባል።
28ጠማማ ሰው ክፋትን ይዘራል፥
የሐሰት መብራት ክፉዎችን ታቃጥላቸዋለች፥
ወዳጆችንም ትለያለች።
29ክፉ ሰው ወዳጆቹን ይዋሻል፥
መልካምም ወዳልሆኑ መንገዶች ይመራቸዋል።
30በዐይኑ ትኩር ብሎ የሚመለከት፥ ጠማማ ዐሳብን ያስባል፤
በከንፈሩም ክፉውን ሁሉ የሚያደርግ የክፋት ምድጃ ነው።
31መልካም ሽምግልና የክብር አክሊል ነው፥
እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።
32ትዕግሥተኛ ሰው ከኀያል፥
ጥበብ ያለው ሰውም ሰፊ ርስት ካለው፥#“ጥበብ ያለው ሰውም ሰፊ ርስት ካለው” የሚለው በግሪኩ የለም።
በመንፈሱ የሠለጠነ ሰውም ሀገርን ከሚገዛ ሰው ይሻላል።
33የበደለኛ ሰው በደሉ ሁሉ ወደ ጕያው ይመለሳል።
ጽድቅ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in