ወደ ሮሜ ሰዎች 15
15
ባልንጀራን ስለ መርዳት
1የሚገባስ እና ብርቱዎች ደካሞችን በድካማቸው እንድንረዳቸው ነው፤ ለራሳችንም አናድላ። 2ሁላችንም በእውነትና በመልካም ሥራ ይታነጽ ዘንድ ለባልንጀራችን እናድላ። 3#መዝ. 68፥9። ክርስቶስም፥ “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ለራሱ ያደላ አይደለም። 4የተጻፈው ሁሉ በመታገሣችንና መጻሕፍትን በመታመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ እና ልንማርበት ተጻፈ። 5የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እግዚአብሔር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ እርስ በርሳችን አንድ ዐሳብ መሆንን ይስጠን። 6ሁላችን አንድ ሆነን በአንድ አፍ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ።#ምዕ. 15 ቍ. 5 እና 6 ግሪኩ በሁለተና መደብ ይጽፋል።
ወንጌልን ለአሕዛብም ለአይሁድም ስለ መስበክ
7አሁንም ባልንጀሮቻችሁን ተቀበሉ፤ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር ተቀብሎአችኋልና። 8እንግዲህ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለማድረግ የአባቶቻችንንም ተስፋ ያጸና ዘንድ ለግዝረት መልእክተና ሆነ እላለሁ። 9#2ሳሙ. 22፥50፤ መዝ. 17፥49። አሕዛብም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ ይቅር ብሎአቸዋልና፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል እገዛልሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ።” 10#ዘዳ. 32፥43። ዳግመናም መጽሐፍ እንዲህ ብሎአል፥ “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።” 11#መዝ. 116፥1። ዳግመናም እንዲህ አለ፥ “አሕዛብ ሁላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያመሰግኑታል።” 12#ኢሳ. 11፥10። ኢሳይያስም ደግሞ እንዲህ ብሎአል፥ “የእሴይ ዘር ይነሣል፤ ከእርሱ የሚነሣውም ለአሕዛብ ንጉሥ ይሆናል፤ ሕዝቡም ተስፋ ያደርጉታል።” 13የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ።
የጳውሎስ ሐዋርያዊ ተልእኮ
14ወንድሞች ሆይ፥ እኔም በጎ ምግባርን ሁሉ እንደምትፈጽሙ እታመንባችኋለሁ፤ እናንተ ፍጹም ዕውቀትን የተመላችሁ ናችሁ፤ ባልንጀሮቻችሁንም ልታስተምሩአቸው ትችላላችሁ። 15ከእግዚአብሔር ስለ አገኘሁት ጸጋ ላሳስባችሁ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። 16በአሕዛብ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን አገለግል ዘንድ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌልም እገዛ ዘንድ፥ በእኔ ትምህርት አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተወደደና የተመረጠ መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ። 17ለእኔም በእግዚአብሔር ዘንድ መመኪያዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 18አሕዛብም እንዲያምኑ ክርስቶስ በቃልም በሥራም ያደረገልኝን እናገር ዘንድ እደፍራለሁ። 19በኀይልና በተአምራት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ድንቅ ሥራን በመሥራትም፥ ከኢየሩሳሌም አውራጃዎች ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እንደ አስተማርሁ፥ የክርስቶስንም ወንጌል ፈጽሞ እንደ ሰበክሁ እናገር ዘንድ እደፍራለሁ። 20ወንጌልን ለማስተማር ተጋሁ፤ ነገር ግን በሌላ መሠረት ላይ እንዳላንጽ የክርስቶስ ስም ወደ ተጠራበት አልሄድሁም። 21#ኢሳ. 52፥15። “ወሬው ያልደረሳቸው ያውቁታል፤ ያልሰሙትም ያስተውሉታል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ነው።
22 #
ሮሜ 1፥13። ዘወትር ወደ እናንተ ልመጣ እወድድ ነበር፤ ነገር ግን ተሳነኝ። 23አሁን ግን በዚህ ሀገር ሥራዬን ስለ ጨረስሁ፥ ከብዙ ጊዜም ጀምሮ ወደ እናንተ ልመጣ እተጋ ስለ ነበር፤ 24ወደ አስባንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ቀደም ብዬ ከእናንተ ጋር ደስ ካለኝ በኋላም ከእናንተ ወደዚያ እሄዳለሁ።
ምእመናንን ስለ መርዳት
25አሁን ግን ቅዱሳንን ለመርዳት ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። 26#1ቆሮ. 16፥1-4። መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ላሉ ድሆች አስተዋጽፅኦ ለማድረግ ተባብረዋልና። 27#1ቆሮ. 9፥11። የሚገባቸውም ሰለሆነ በመንፈሳዊ ሥራ አሕዛብን ከተባበሩአቸው ለሰውነታቸው በሚያስፈልጋቸው ሊረዱአቸው ይገባል። 28እንግዲህ ይህን ፍሬ ጨርሼና አትሜ በእናንተ በኩል ወደ አስባንያ እሄዳለሁ። 29ነገር ግን በመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ወንጌል በረከት ፍጹምነት እንደምትመጣ አምናለሁ።
30ወንድሞች፥ በጸሎታችሁ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ትተጉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እማልዳችኋለሁ። 31ይኸውም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳንን በአገልግሎቴ ደስ አሰናቸው ዘንድ በይሁዳ ሀገር ካሉ ዐላውያን እንዲያድነኝ ነው። 32እግዚአብሔርም ቢፈቅድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር ዐርፍ ዘንድ ነው። 33የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 15: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in