1 የጴጥሮስ መልእክት 4
4
1-2ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና። 3የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና። 4በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ፤ 5ግን እነርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6እንደሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባችው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና።
7ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥ 8ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 9ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤ 10ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 11ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።
12ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ 13ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። 14ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። 15ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ 16ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። 17ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው? 19ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።
Currently Selected:
1 የጴጥሮስ መልእክት 4: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in