አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1
1
1በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፥ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ። 2ሁለትም ሚስቶች ነበሩት የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፥ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም። 3ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ። 4ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው። 5ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት፥ 6እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር። 7በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፥ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር። 8ባልዋም ሕልቃና፦ ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት። 9በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሐና ተነሳች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። 10እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔርም ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች። 11እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። 12ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፍዋን ይመለከት ነበር። 13ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፥ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፥ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። 14ዔሊም፦ ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት። 15ሐናም፦ ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፥ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፥ 16ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት። 17ዔሊም፦ በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት። 18እርስዋም፦ ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች፥ በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።
19ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፥ እግዚአብሔርም አሰባት፥ 20የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፥ እርስዋም፦ ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው።
21ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ። 22ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም፦ ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፥ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው። 23ባልዋም ሕልቃና፦ በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፥ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች። 24ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፥ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ። 25ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት። 26እርስዋም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። 27ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፥ 28እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፥ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in