ኦሪት ዘዳግም 18
18
1ለሌዋውያን ካህናት፥ ለሌዊም ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር ድርሻና ርስት አይሆንላቸውም፤ በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕቱንና ርስቱን ይበላሉ። 2በወንድሞቻቸውም መካከል ርስት አይሆንላቸውም፤ እርሱ እንደተናገራቸው ርስታቸው እግዚአብሔር ነው። 3በሬ ወይም በግ ለመሥዋዕት ከሚያቀርቡት ሕዝብ የካህናቱ ወግ ይህ ይሆናል፤ ወርቹንና ሁለቱን ጉንጮቹን ጨጓራውንም ለካህኑ ይሰጣሉ። 4የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም በኩራት፥ አስቀድሞም የተሸለተውን የበግህን ጠጉር ለእርሱ ትሰጣለህ። 5እርሱ ከልጆቹ ጋር ተነሥቶ በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ሁሉ ስለ መረጠው ነው። 6አንድ ሌዋዊ ሰው ከሚቀመጥባቸው በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ካሉት ከአገር ደጆች ከአንዲቱ ቢወጣ፥ በፍጹም ፈቃድም እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ቢመጣ፥ 7በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙት እንደ ወንድሞቹ እንደ ሌዋውያን ሁሉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ያገለግላል። 8ከተሸጠው ከአባቶቹ ከብት ዋጋ ሌላ እንደ ባልንጀሮቹ ከመብል ድርሻውን ይወስዳል። 9አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኩሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። 10ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ 11አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቁልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቍይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። 12ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኩሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል። 13አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን። 14የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከልክሎሃል። 15-16አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን፦ እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔር ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ። 17እግዚአብሔርም አለኝ፦ የተናገሩት መልካም ነው፤ 18ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ 19በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ። 20ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል። 21በልብህም፦ እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ 22ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 18: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in