YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1

1
1ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ 2ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ 3እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ 4ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል።
5ከመላእክትስ፦
አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥
ደግሞም፦
እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል
6ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦
የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ
ይላል። 7ስለ መላእክትም፦
መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ
8ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፦
አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤
የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።
9ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር
አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ
10ይላል። ደግሞ፦
ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥
ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤
11እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም
እንደ ልብስ ያረጃሉ፥
12እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም
13ይላል። ነገር ግን ከመላእክት፦
ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ
14ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1