YouVersion Logo
Search Icon

የሉቃስ ወንጌል 8

8
1ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤ 2አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ 3የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።
4ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ 5ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት። 6ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። 7ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። 8ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ፦ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ።
9ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። 10እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። 11ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። 12በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። 13በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። 14በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። 15በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
16መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። 17የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። 18እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።
19እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፥ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልተቻላቸውም። 20እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ወድደው በውጭ ቆመዋል ብለው ነገሩት። 21እርሱም መልሶ፦ እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።
22ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም። 23ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር። 24ቀርበውም፦ አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጽጥታም ሆነ። 25እርሱም፦ እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፦ እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።
26በገሊላም አንጻር ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በታንኳ ደረሱ። 27ወደ ምድርም በወጣ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፥ ከብዙ ዘመንም ጀምሮ ልብስ ሳይለብስ በመቃብር እንጂ በቤት አይኖርም ነበር። 28ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ። 29ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር። 30ኢየሱስም፦ ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና፦ ሌጌዎን አለው። 31ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት። 32በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም። 33አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።
34እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት። 35የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። 36ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። 37በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ። 38አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤ 39ነገር ግን፦ ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
40ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት። 41እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤ 42አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች።
ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር። 43ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም። 44በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ። 45ኢየሱስም፦ የዳሰሰኝ ማን ነው? አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት፦ አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን? አሉ። 46ኢየሱስ ግን፦ አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ። 47ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች። 48እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።
49እርሱም ገና ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ፦ ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም አለ። 50ኢየሱስ ግን ሰምቶ፦ አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች ብሎ መለሰለት። 51ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም። 52ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፦ አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ። 53እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት። 54እርሱ ግን እጅዋን ይዞ፦ አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ ብሎ ጮኸ። 55ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ። 56ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in