YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኊልቊ 35

35
1እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰምርያ ለሌዋውያን ስጡ። 3እነርሱም በከተሞቹ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ መሰምርያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም ለእነርሱም ላለው ሁሉ ይሁን። 4ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰምርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን። 5ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰምርያ ይሆንላቸዋል። 6ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ። 7ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰምርያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ። 8ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ። 9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ 11በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ። 12ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 13የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 14በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። 15በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። 16በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 17ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 18ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 19ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኛው ጊዜ ይግደለው። 20እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 21ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። 22ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 23ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥ 24ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤ 25ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። 26ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥ 27ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ 28ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። 29እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። 30ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። 31ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 32ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። 33ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። 34እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in