YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ሩት 3

3
ሩት ባል እንዳገኘች
1አማትዋም ኑኃሚን አለቻት “ልጄ ሆይ! መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? 2አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ትበትናል። 3እንግዲህ ታጠቢ፤ ተቀቢ፤ ልብስሽን ተላበሺ፤ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። 4በትኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፤ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፤ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።” 5ሩትም “የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤” አለቻት።
6ወደ አውድማውም ወረደች፤ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። 7ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፤ እግሩንም ገልጣ ተኛች። 8መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፤ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። 9እርሱም “ማን ነሽ?” አለ። እርስዋም “እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ፤” አለችው። 10ቦዔዝም አላት “ልጄ ሆይ! በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። 11አሁንም፥ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ። 12የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ። 13ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፤ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ።”
14እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም “ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ፤” ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች። 15እርሱም “የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው፤” አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት፤ አሸከማትም። 16እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፤ አማትዋም “ልጄ ሆይ! እንዴት ነሽ?” አለቻት፤ እርስዋም ስውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት። 17“‘ወደ አማትሽም ባዶ እጅሽን አትሂጂ፤’ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ፤” አለቻት። 18እርስዋም “ልጄ ሆይ! ስውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ፤” አለች።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in