YouVersion Logo
Search Icon

ሐዋርያት ሥራ 19

19
ጳውሎስ በኤፌሶን
1አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር ዐልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አግኝቶ፣ 2“ባመናችሁ#19፥2 ወይም ካመናችሁ በኋላ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው።
እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት።
3ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው።
እነርሱም፣ “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት።
4ጳውሎስም፣ “የዮሐንስ ጥምቀትማ የንስሓ ጥምቀት ነበር፤ ዮሐንስም ራሱ ሰዎች ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ እንዲያምኑ ተናግሯል” አላቸው። 5እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። 6ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች#19፥6 ወይም ልሳን ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። 7ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ።
8ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር። 9አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር። 10ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።
11እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤ 12መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቅቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።
13እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዝዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኩሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤ 14የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር። 15ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው። 16ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘልሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቍታቸውን ሸሹ።
17ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ። 18ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ ተናዘዙ፤ 19ሲጠነቍሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ አምሳ ሺሕ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ። 20በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
21ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ። 22ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።
በኤፌሶን የተነሣው ሁከት
23በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ። 24ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም። 25እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ። 26ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና። 27የዚህ የሥራችን መልካም ስም ከመጕደፉም በላይ፣ መላው እስያና ዓለም የሚያመልካት የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስም ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ደግሞም ገናናው ክብሯ ይዋረዳል።”
28ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጥተው፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር። 29ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋር ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ። 30ጳውሎስም ወጥቶ ሕዝቡ ፊት ለመቅረብ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከለከሉት። 31ከአውራጃው ባለ ሥልጣናት አንዳንድ ወዳጆቹ እንኳ፣ ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ደፍሮ እንዳይገባ ሰው ልከው ለመኑት።
32ጉባኤውም ተበጣብጦ፣ አንዱ አንድ ነገር ሲናገር ሌላውም ሌላ እየተናገረ ይጯጯኽ ነበር፤ አብዛኛውም ሰው ለምን እዚያ እንደ ተሰበሰበ እንኳ አያውቅም ነበር። 33አይሁድም እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ገፍተው ወደ ፊት ባወጡት ጊዜ፤ አንዳንዶቹ እንዲናገርላቸው ጮኹ፤ እርሱም ሊከራከርላቸው ፈልጎ ዝም እንዲሉ በምልክት ጠቀሳቸው። 34ነገር ግን እርሱ አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
35የከተማዪቱም ዋና ጸሓፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፤ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፤ የታላቋ የአርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶን ከተማ ሕዝብ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ? 36ስለዚህ፣ ይህ ሐቅ የማይካድ እንደ መሆኑ መጠን፣ ልትረጋጉና አንዳች ነገር በጥድፊያ ከመፈጸም ልትቈጠቡ ይገባችኋል። 37እነዚህን ሰዎች ቤተ መቅደስን ሳይዘርፉ ወይም አምላካችን በሆነችው ላይ የስድብ ቃል ሳይሰነዝሩ ይዛችሁ እዚህ ድረስ እንዲያው አምጥታችኋቸዋል። 38እንግዲህ፣ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች በማንም ላይ አቤቱታ ካላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክፍት ነው፤ ዳኞችም አሉ፤ ክስ ማቅረብ ይችላሉ። 39ከዚህ ሌላ ልታቀርቡ የፈለጋችሁት ነገር ካለ በሕጋዊ ጉባኤ ይታያል። 40አለዚያ ዛሬ ስለ ሆነው ነገር፣ በሁከት አነሣሽነት እንዳንከሰስ ያሠጋናል፤ አጥጋቢ ምክንያት ስለሌለንም፣ ስለ ሁከቱ ብንጠየቅበት መልስ መስጠት አንችልም።” 41ይህን ከተናገረ በኋላም ጉባኤው እንዲበተን አደረገ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ሐዋርያት ሥራ 19