YouVersion Logo
Search Icon

ዮሐንስ 16

16
1 “ይህን ሁሉ የነገርኋችሁ እንዳትሰናከሉ ነው። 2ከምኵራብ ያስወጧችኋል፤ እንዲያውም የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳገለገለ የሚቈጥርበት ጊዜ ይመጣል። 3ይህን ሁሉ የሚያደርጉባችሁ፣ አብን ወይም እኔን ስላላወቁ ነው። 4አስቀድሜ ይህን የነገርኋችሁ ጊዜው ሲደርስ እንድታስታውሱ ነው፤ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርሁ፣ ይህን ከመጀመሪያው አልነገርኋችሁም።
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ
5 “እንግዲህ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ፣ ‘የምትሄደው የት ነው?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል፤ 7ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ 8በሚመጣበትም ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአት#16፥8 ወይም የዓለምን ኀጢአት ይገልጣል፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሣል። 9ስለ ኀጢአት ሲባል፣ ሰዎች በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ 10ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ 11ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።
12 “ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። 13የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ 14የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። 15የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።
16 “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።”
የደቀ መዛሙርት ሐዘን ወደ ደስታ መለወጥ
17ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “  ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤ 18“  ‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር።
19ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደ ሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ? 20እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች፤ 22ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 24እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል።
25 “እስከ አሁን የነገርኋችሁ በምሳሌ ቢሆንም እንኳ፣ ከእንግዲህ ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል። 26በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ 27ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወድዳችኋል። 28ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ አሁን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ።”
29ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አሁንም እኮ ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርህ ነው። 30አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ ተረድተናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እንድናምን አድርጎናል።”
31ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው?#16፥31 ወይም በስተ መጨረሻው አመናችሁ! 32እነሆ፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጊዜ አሁን ነው። እኔንም ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፤ ይሁን እንጂ አባቴ ከእኔ ጋር ስለሆነ ብቻዬን አይደለሁም።
33 “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”

Currently Selected:

ዮሐንስ 16: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in