ሉቃስ 17
17
ኀጢአት፣ እምነት፣ ኀላፊነት
1ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎችን የሚያሰናክል መምጣቱ አይቀርም፤ ነገር ግን ለመሰናክሉ መምጣት ምክንያት ለሚሆን ለዚያ ሰው ወዮለት። 2ይህ ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል፣ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። 3ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
“ወንድምህ ቢበድል ገሥጸው፤ ቢጸጸት ይቅር በለው። 4በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ፣ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ ይቅር በለው።”
5ሐዋርያትም ጌታን፣ “እምነታችንን ጨምርልን” አሉት።
6ጌታም፣ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ፣ ‘ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ተተከል’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው።
7ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ዐራሽ ወይም በግ ጠባቂ የሆነ አገልጋይ ቢኖረው፣ ከዕርሻ የተመለሰውን አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ወደ ማእድ ቅረብ’ ይለዋልን? 8ከዚህ ይልቅ፣ ‘እራቴን እንድበላ አዘጋጅልኝ፣ እኔ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፤ ትጠጣለህ’ አይለውምን? 9እንግዲህ ይህ ሰው፣ አገልጋዩ የታዘዘውን በመፈጸሙ መልሶ ያመሰግነዋልን? 10ስለዚህ እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፣ ‘ከቍጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ።’ ”
ከለምጽ የነጹ ዐሥር ሰዎች
11ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኩል ዐለፈ፤ 12ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ#17፥12 የግሪኩ ቃል ከለምጽ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ 13በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት።
14እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ።
15ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ 16በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።
17ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? 18ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?” 19ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።
የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት
17፥26፡27 ተጓ ምብ – ማቴ 24፥37-39
20ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ 21ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ#17፥21 ወይም በውስጣቸው ናትና።”
22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። 23ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ 24ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። 25ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል።
26 “በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። 27ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።
28 “በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ 29ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።
30 “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። 31በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ፣ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። 32የሎጥን ሚስት አስታውሱ። 33ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል። 34እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። 35ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። 36ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ አብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”#17፥36 አንዳንድ ቅጆች ቍጥር 36 የላቸውም።
37እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት።
እርሱም፣ “ጥንብ ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።
S'ha seleccionat:
ሉቃስ 17: NASV
Subratllat
Comparteix
Copia
Vols que els teus subratllats es desin a tots els teus dispositius? Registra't o inicia sessió
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.