ዮሐንስ 18
18
ኢየሱስ በተቃዋሚዎቹ መያዙ
18፥3-11 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥47-56፤ ማር 14፥43-50፤ ሉቃ 22፥47-53
1ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ።
2ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። 3ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር።
4ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው።
5እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።
ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።
7እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።
8ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ 9ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።
10ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ይባል ነበር።
11ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው።
ኢየሱስ በሊቀ ካህናቱ በሐና ፊት ቀረበ
18፥12፡13 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥57
12ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ ሎሌዎች ጋር በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣ 13በመጀመሪያ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር። 14ቀያፋም ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር።
የጴጥሮስ ክሕደት
18፥16-18 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥69፡70፤ ማር 14፥66-68፤ ሉቃ 22፥55-57
15ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ 16ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ።
17በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው።
እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ።
18ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።
ኢየሱስ በሊቀ ካህናቱ ፊት መቅረቡ
18፥19-24 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥59-68፤ ማር 14፥55-65፤ ሉቃ 22፥63-71
19በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።
20ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። 21ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።”
22ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው።
23ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።#18፥24 ወይም ሐናም ወደ ቀያፋ እንደ ታሰረ ላከው
የጴጥሮስ ሁለተኛና ሦስተኛ ክሕደት
18፥25-27 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥71-75፤ ማር 14፥69-72፤ ሉቃ 22፥58-62
25ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት።
እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል ካደ።
26ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከእርሱ ጋር አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው። 27ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት
18፥29-40 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥11-18፡20-23፤ ማር 15፥2-15፤ ሉቃ 23፥2፡3፡18-25
28አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም። 29ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው።
30እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት።
31ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።
አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት። 32ይህ የሆነው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።
33ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።
34ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት።
35ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው።
36ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው።
37ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው።
ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው።
38ጲላጦስም፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለው፤ ይህን ከተናገረ በኋላም እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ የሚያስከስስ በደል አላገኘሁበትም፤ 39ነገር ግን በፋሲካ አንድ እስረኛ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ ስለዚህ፣ ‘የአይሁድን ንጉሥ’ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?”
40እነርሱም እንደ ገና በመጮኽ፣ “የለም፤ እርሱን አይደለም! በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።
Právě zvoleno:
ዮሐንስ 18: NASV
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.