ኦሪት ዘፍጥረት 14
14
1በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን 2እንዲህ ሆነ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንግሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ። 3እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። 4አሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። 5በአሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይ፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፤ 6የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። 7ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፤ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴሶን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ። 8የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤ 9የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፤ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፤ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ። 10በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍር ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹ። 11የሰዶምንና የገሞራንን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። 12በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።
13አንድ የሸሸ ስውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የአድባር ዛፍ ይኖር ነበር። 14አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተለትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። 15ብላቴኖቹንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። 16ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።
17ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለስ በኍላም የሰዶም ንጉሥ ሸለቆ በሆን በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። 18የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። 19ባረከውም፤ አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ 20ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው። 21የሰዶም ንጉሥም አብራምን፤ ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው። 22አብራምም የስዶምን ንጉሥ አለው፤ ሰማይንና ምድርን ወደ ሚግዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ 23አንተ፤ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ 24ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ ቢሆን ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፤ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ።
Dewis Presennol:
ኦሪት ዘፍጥረት 14: አማ54
Uwcholeuo
Rhanna
Copi
Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda