Logo YouVersion
Eicon Chwilio

የሉቃስ ወንጌል 23

23
1ሁሉም በሞላው ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና፦ 2ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። 3ጲላጦስም፦ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ፦ አንተ አልህ አለው። 4ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፦ በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። 5እነርሱ ግን አጽንተው፦ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ።
6ጲላጦስ ግን፦ ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ፦ የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፤ 7ከሄሮድስም ግዛት እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና። 8ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። 9በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም። 10የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው ሲከሱት ቆመው ነበር። 11ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፥ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። 12ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፥ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና።
13ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ 14ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። 15ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ 16-17እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ። በበዓሉ አንድ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና።
18ሁላቸውም በአንድነት፦ ይህን አስወግድ፥ በርባንንም ፍታልን እያሉ ጮኹ፤ 19እርሱም ሁከትን በከተማ አንሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። 20ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወድዶ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ 21ነገር ግን እነርሱ፦ ስቀለው ስቀለው እያሉ ይጮኹ ነበር። 22ሦስተኛም፦ ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው። 23እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጽንተው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ። 24ጲላጦስም ልመናቸው እንዲሆንላቸው ፈረደበት። 25ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።
26በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። 27ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። 28-29ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። 30በዚያን ጊዜ ተራራዎችን፦ በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም፦ ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ 31በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?
32ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ። 33ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። 34ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። 35ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ፦ ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። 36ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው፦ 37አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። 38ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ።
39ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። 40ሁለተኛው ግን መልሶ፦ አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? 41ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። 42ኢየሱስንም፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። 43ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።
44ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ 45የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። 46ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። 47የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። 48ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። 49የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር።
50እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ 51ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። 52ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ 53አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። 54የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። 55ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። 56ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ።
በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።

Uwcholeuo

Rhanna

Copi

None

Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda