ሐዋርያት ሥራ 12
12
ጴጥሮስ ከእስር ቤት በታምር ወጣ
1በዚያ ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላትን እያሳደደ ያስጨንቅ ነበር፤ 2የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለ። 3ይህ አድራጎቱ አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ፣ ጴጥሮስን ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው በቂጣ በዓል ሰሞን ነበር። 4ጴጥሮስን ወህኒ ቤት ካስገባው በኋላ፣ አራት አራት ወታደሮች እየሆኑ እንዲጠብቁት በአራት ፈረቃ ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገውም የፋሲካ በዓል ካለፈ በኋላ ሕዝብ ፊት አውጥቶ ሊያስፈርድበት አስቦ ነው።
5ጴጥሮስም በዚህ መሠረት እስር ቤት ተጣለ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ስለ እርሱ አጥብቃ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር።
6ሄሮድስም ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው አስቦ ሳለ፣ ጴጥሮስ በዚያው ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ፣ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም እስር ቤቱ በር ላይ ቆመው ነበር። 7የጌታ መልአክም ድንገት ታየ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩም የጴጥሮስን ጐን መታ አድርጎ ቀሰቀሰውና፣ “ቶሎ ተነሣ!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ሰንሰለቶቹ ከእጆቹ ወደቁ።
8መልአኩም፣ “ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። ጴጥሮስም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም ቀጥሎ፣ “መደረቢያህን ከላይ ጣል አድርገህ ተከተለኝ” አለው። 9ጴጥሮስም ተከትሎት ከእስር ቤት ወጣ፤ ነገር ግን ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ የሚያደርገው ነገር በእውን መሆኑን አላወቀም ነበር። 10የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ ዐልፈው ወደ ከተማዪቱ በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለው የብረት መዝጊያ ዘንድ ደረሱ። መዝጊያውም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ሄዱ፤ አንዲት ስላች መንገድ እንዳለፉም ወዲያው መልአኩ ተለየው።
11ጴጥሮስም ሲረጋጋ፣ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ።
12ይህን ከተረዳ በኋላም፣ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአንድነት ወደሚጸልዩበት፣ ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። 13እዚያ ደርሶ የውጭውን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ማን እንደ ሆነ ለማጣራት ወደ በሩ ሄደች። 14የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ፣ በጣም ከመደሰቷ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ በመመለስ፣ ጴጥሮስ በሩ ላይ ቆሞ እንደሚገኝ ተናገረች።
15ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የእርሱ መልአክ ነው” አሉ።
16ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። 17እርሱም ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ፣ ጌታ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው አስረዳቸው፣ “ስለ ሁኔታው ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው፤ ከዚያም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
18በማግስቱም ጧት ወታደሮቹ፣ “ጴጥሮስ የት ገባ?” እያሉ በመካከላቸው ትልቅ ትርምስ ተፈጠረ። 19ሄሮድስም ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ፣ ዘብ ጠባቂዎቹን በጥብቅ ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ።
የሄሮድስ አሟሟት
ከዚያም ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ እዚያ ተቀመጠ። 20እርሱም ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋር ጥለኛ ነበር፤ አገራቸው ምግብ የሚያገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለ ነበር፣ የንጉሡን ባለሟል የብላስጦስን ድጋፍ ካገኙ በኋላ፣ አንድ ላይ ሆነው ከንጉሡ ጋር ለመታረቅ ጠየቁ።
21በቀጠሮውም ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ንግግር አደረገ። 22ሕዝቡም፣ “ይህስ የአምላክ ድምፅ እንጂ የሰው አይደለም” ብለው ጮኹ። 23ሄሮድስም ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ የጌታ መልአክ ወዲያው መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ።
24የእግዚአብሔር ቃል ግን እያደገና እየሰፋ ሄደ።
25በርናባስና ሳውልም ተልእኳቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም#12፥25 አንዳንድ ቅጆች ወደ ኢየሩሳሌም ይላሉ። ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።
Attualmente Selezionati:
ሐዋርያት ሥራ 12: NASV
Evidenziazioni
Condividi
Copia
Vuoi avere le tue evidenziazioni salvate su tutti i tuoi dispositivi?Iscriviti o accedi
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.