Logo YouVersion
Icona Cerca

ሐዋርያት ሥራ 27

27
ጳውሎስ በመርከብ ወደ ሮም ተወሰደ
1ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው። 2ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጕዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ።
3በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት። 4ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለ ገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን። 5በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን። 6ከዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። 7ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤ 8ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ “መልካም ወደብ” ወደ ተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን።
9ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ#27፥9 የስርየትን ዕለት ያሳያል። በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣ 10“እናንት ሰዎች፤ ጕዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጕዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው። 11የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር። 12ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጕዟችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር።
የባሕሩ ማዕበል
13መጠነኛ የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው፣ የቀርጤስን ዳርቻ በመያዝ ተጓዙ። 14ብዙም ሳይቈይ ግን፣ “ሰሜናዊ ምሥራቅ” የሚሉት ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ቍልቍል መጣባቸው። 15መርከቢቱም በማዕበሉ ስለ ተያዘች፣ ወደ ነፋሱ መግፋት አልቻለችም፤ ስለዚህ መንገድ ለቅቀን በነፋሱ ተነዳን። 16ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በማለፍ፣ የመርከቧን ሕይወት አድን ጀልባ በብዙ ድካም ለማትረፍ ቻልን፤ 17ጀልባዋንም ወደ ላይ ጐትተው ካወጧት በኋላ መርከቧ እንዳትፈራርስ ዙሪያዋን በገመድ ጠምጥመው አሰሯት፤ ስርቲስ ከተባለው አሸዋማ ደለል ጋር ሄደው እንዳይላተሙ ስለ ፈሩም፣ የመርከቧን ሸራ አውርደው እንዲሁ በዘፈቀደ እንድትነዳ አደረጉ። 18ማዕበሉም ክፉኛ ስላንገላታን፣ በማግስቱም ጭነቱን እያነሡ ወደ ባሕር ይጥሉ ጀመር፤ 19በሦስተኛውም ቀን፣ የመርከቧን ሸራ ማውጫና ማውረጃ መሣሪያ በገዛ እጃቸው ነቃቅለው ወደ ባሕር ጣሉት። 20ብዙ ቀን፣ ፀሓይንም ከዋክብትንም ማየት ስላልተቻለና ነፋስ ስለ በረታብን፣ ለመትረፍ የነበረን ተስፋ ሁሉ ተሟጠጠ።
21ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ፣ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንት ሰዎች ሆይ፤ የነገርኋችሁን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከቀርጤስ ባልተነሣችሁና ይህ ጕዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁ ነበር። 22አሁንም ቢሆን አይዟችሁ፤ መርከቧ እንጂ ከእናንተ አንዲት ነፍስ እንኳ አትጠፋምና። 23በትላንትናዋ ሌሊት፣ የእርሱ የሆንሁትና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ፣ 24‘ጳውሎስ ሆይ፤ አትፍራ፤ በቄሳር ፊት መቆም ይገባሃል፤ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሰዎች ሕይወት እግዚአብሔር አትርፎልሃል’ አለኝ። 25ስለዚህ፣ እናንት ሰዎች ሆይ፤ አይዟችሁ እርሱ እንደ ነገረኝ እንደዚያው እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና። 26ይሁን እንጂ፣ ወደ አንዲት ደሴት በነፋስ ተወስደን እዚያ መጣላችን አይቀርም።”
በመርከቡ አደጋ መድረሱ
27በዐሥራ አራተኛው ሌሊት በአድርያ#27፥27 በጥንት ጊዜ ይህ ስም ሰፊውን የኢጣሊያ ደቡባዊ ክፍል ያመለክታል። ባሕር ላይ ከወዲያ ወዲህ ስንገላታ፣ እኩለ ሌሊት ገደማ መርከበኞቹ ወደ መሬት የተቃረቡ መሰላቸው፤ 28የጥልቀት መለኪያውን ገመድ ወደ ታች ጥለው ሲመለከቱት የውሃው ጥልቀት አርባ ሜትር ያህል ሆኖ አገኙት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ደግመው ሲጥሉ ጥልቀቱ፣ ሠላሳ ሜትር ያህል ሆነ። 29ከቋጥኞቹም ጋር እንዳንላተም በመፍራት፣ አራት መልሕቆች ከመርከቡ በስተ ኋላ ጣሉ፤ ምነው በነጋ እያሉም ይለምኑ ነበር። 30መርከበኞቹም ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ የሚጥሉ መስለው፣ ትንሿን ጀልባ በማውረድ ከመርከቧ ሊያመልጡ ሞከሩ። 31ጳውሎስም የመቶ አለቃውንና ወታደሮቹን፣ “እነዚህ ሰዎች መርከቡ ላይ ካልቈዩ እናንተም ልትተርፉ አትችሉም” አላቸው። 32በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ገመዶቹን ቈርጠው ትንሿ ጀልባ ባሕሩ ላይ ተንሳፍፋ እንድትቀር ለቀቋት።
33ልክ ሊነጋጋ ሲል፣ ጳውሎስ ሁሉም ምግብ እንዲበሉ እንዲህ ሲል ለመናቸው፤ “ዐሥራ አራት ቀን ሙሉ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ምንም ሳትቀምሱ ጦማችሁን ሰነበታችሁ፤ 34ስለዚህ፣ ስለሚያበረታችሁ አሁን እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋላሁ፤ ከእናንተ መካከል ከራሱ ጠጕር አንዲት እንኳ የሚነካበት ማንም የለምና።” 35ይህን ካለ በኋላም፣ እንጀራ ይዞ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ጀመር። 36ሁሉም ተበራቱና እንጀራውን ራሳቸው ወስደው በሉ። 37በመርከቡም ላይ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሰዎች ነበርን። 38በልተውም ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕር በመጣል የመርከቡን ክብደት አቃለሉ።
39በነጋም ጊዜ፣ ወደ የብስ መቅረባቸውን አላወቁም ነበር፤ ነገር ግን ዳር ዳሩ አሸዋማ የሆነ የባሕር ሰርጥ አይተው፣ ቢቻላቸው መርከቡን ገፍተው ወደዚያ ለማድረስ ወሰኑ። 40ከዚያም መልሕቆቹን ቈርጠው ባሕር ውስጥ ጥለው ሄዱ፤ የመቅዘፊያውንም ገመድ በዚያው ጊዜ ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ባሕሩ ዳርቻ አቀኑ። 41ነገር ግን መርከቡ ከአሸዋ ቍልል ጋር ተላትሞ መሬት ነካ፤ የፊተኛው ክፍሉም አሸዋው ውስጥ ተቀርቅሮ አልነቃነቅ አለ፤ የኋለኛው ክፍሉም በማዕበሉ ክፉኛ ስለ ተመታ ይሰባበር ጀመር።
42ወታደሮቹም ከእስረኞች ማንም ዋኝቶ ለማምለጥ ቢሞክር ለመግደል ተስማሙ። 43የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ እንዲተርፍ ስለ ፈለገ፣ ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው፤ መዋኘት የሚችሉ ከመርከብ እየዘለሉ አስቀድመው ከባሕሩ ወደ ምድር እንዲወጡ፣ 44የተቀሩት ደግሞ በሳንቃዎች ወይም በመርከቡ ስብርባሪ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።

Attualmente Selezionati:

ሐዋርያት ሥራ 27: NASV

Evidenziazioni

Condividi

Copia

None

Vuoi avere le tue evidenziazioni salvate su tutti i tuoi dispositivi?Iscriviti o accedi