ኦሪት ዘፍጥረት 11
11
የሰናዖር ግንብ
1የዓለም ሁሉ ቋንቋ አንድ፥ ንግግሩም አንድ ነበረ። 2እንዲህም ሆነ፤ ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ። 3እርስ በርሳቸውም፥ “ኑ ጡብ እንሥራ፤ በእሳትም እንተኵሰው” ተባባሉ። ጡባቸውም እንደ ድንጋይ፥ ጭቃቸውም እንደ ዝፍት ሆነላቸው። 4እርስ በርሳቸውም፥ “ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ሳንበተን ስማችንን እናስጠራው” ተባባሉ። 5እግዚአብሔርም የሰዎች ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። 6እግዚአብሔርም አለ፥ “እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፤ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ መሥራትን አይተዉም። 7ኑ እንውረድ፤ አንዱ የሌላውን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።” 8እግዚአብሔርም ቋንቋቸውን ለያየ፤#“እግዚአብሔርም ቋንቋቸውን ለያየ” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ከዚያም በምድር ፊት ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከተማዪቱንና ግንቡን መሥራትን ተዉ። 9ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፤ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቆአልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ፊት ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።
የሴም ትውልድ
(1ዜ.መ. 1፥24-27)
10የሴም ትውልድ ይህ ነው። ሴም ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት አርፋክስድን በወለደ ጊዜ የመቶ ዓመት ሰው ነበረ። 11ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
12አርፋክስድም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፤ ቃይናንንም ወለደ፤ 13አርፋክስድም ቃይናንን ከወለደ በኋላ አራት መቶ አርባ ዓመት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አራት መቶ ሠላሳ” ዕብ. “አራት መቶ” ይላል። ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። ቃይናንም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ ሳላንም ወለደ፤ ቃይናንም ሳላን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ#ዕብ. “ሦስት መቶ ሠላሳ” ይላል። ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ልጆች ወለደ፤ ሞተም።
14ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ ዔቦርንም ወለደ፤ 15ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ ሊ. “ሦስት መቶ ሠላሳ” ይላል። ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
16ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፤ ፋሌቅንም ወለደ፤ 17ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሦስት መቶ ሰባ” ይላል። ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
18ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ ራግውንም ወለደ፤ 19ፋሌቅም ራግውን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
20ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፤ ሴሮሕንም ወለደ፤ 21ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
22ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ ናኮርንም ወለደ፤ 23ሴሮሕም ናኮርን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
24ናኮርም መቶ ዘጠኝ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መቶ ሰባ ዘጠኝ” ይላል። ዓመት ኖረ፤ ታራንም ወለደ፤ 25ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሀያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፤ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
የታራ ትውልድ
26ታራም መቶ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰባ” ይላል። ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን፥ አራንንም ወለደ። 27አራንም ሎጥን ወለደ።#ዕብ. “የታራም ትውልድ ይህ ነው ታራ አብራምንና ናኮርን፥ አራንንም ወለደ” ይላል። 28አራንም በተወለደባት ሀገር በከለዳውያን ምድር#ዕብ. “ዑር” ይላል። በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። 29አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮርም ሚስት የአራን ልጅ ሚልካ ናት፤ አራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው። 30ሦራም መካን ነበረች፤ ልጆችም አልነበሩአትም። 31ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የአራንን ልጅ ሎጥን፥ የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ምድር አወጣቸው። ወደ ካራንም መጡ፤ በዚያም ተቀመጡ። 32ታራም በካራን ምድር የኖረበት ዘመን ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።
Одоогоор Сонгогдсон:
ኦሪት ዘፍጥረት 11: አማ2000
Тодруулга
Хуваалцах
Хувилах
Тодруулсан зүйлсээ бүх төхөөрөмждөө хадгалмаар байна уу? Бүртгүүлэх эсвэл нэвтэрнэ үү