YouVersion လိုဂို
ရှာရန် အိုင်ကွန်

ማርቆስ 16

16
ትንሣኤው
16፥1-8 ተጓ ምብ – ማቴ 28፥1-8ሉቃ 24፥1-10
1ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። 2በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጧት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ 3“ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
4ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባልሎ አዩ። 5ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጕልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።
6እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቷል፤ እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። 7ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።”
8ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም።
9በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት በመጀመሪያ ታየ። 10እርሷም ሄዳ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩት እያዘኑ ሲያለቅሱ አግኝታ፣ 11እርሱ ሕያው መሆኑንና ለእርሷም መታየቱን ነገረቻቸው፤ እነርሱ ግን አላመኗትም።
12ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ታያቸው። 13እነርሱም ተመልሰው ይህንኑ ለቀሩት ነገሯቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱንም አላመኗቸውም።
14ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማእድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። 15እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ 16ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 17የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ 18እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።”
19ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።#16፥20 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከ9-20 ያለው ክፍል የላቸውም።

လက်ရှိရွေးချယ်ထားမှု

ማርቆስ 16: NASV

အရောင်မှတ်ချက်

မျှဝေရန်

ကူးယူ

None

မိမိစက်ကိရိယာအားလုံးတွင် မိမိအရောင်ချယ်သောအရာများကို သိမ်းဆည်းထားလိုပါသလား။ စာရင်းသွင်းပါ (သို့) အကောင့်ဝင်လိုက်ပါ