ዮሐንስ 12
12
ኢየሱስ በቢታንያ ሽቱ መቀባቱ
12፥1-8 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥6-13፤ ማር 14፥3-9፤ ሉቃ 7፥37-39
1የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ። 2በዚያም ለኢየሱስ ሲባል እራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከእርሱ ጋር በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር። 3ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር#12፥3 በግሪኩ ሊትራን ይላል። ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በጠጕሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዓዛ ሞላው።
4ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤ 5“ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” 6ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቍሮ አልነበረም።
7ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለሆነ እንድታቈየው ተዋት፤ 8ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።”
9በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። 10ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤ 11ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።
ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ
12፥12-15 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥4-9፤ ማር 11፥7-10፤ ሉቃ 19፥35-38
12በማግስቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤ 13የዘንባባም ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤
“ሆሣዕና!”#12፥13 በዕብራይስጡ አድን! ማለት ሲሆን፣ የምስጋና ድምፅ ነው።
“በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው!”
“የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!”
14ኢየሱስም የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
15“የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤
እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል
ተቀምጦ ይመጣል።”
16ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለእርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር።
17አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ ነበር። 18ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። 19ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።
ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ
20ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ። 21እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት። 22ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት።
23ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሷል፤ 24እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25ሕይወቱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።
27 “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚህች ሰዓት ብታድነኝስ? ይሁን፤ የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። 28አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው።”
ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። 29በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ።
30ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤ 31ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል። 32እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።” 33ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር።
34ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ#12፥34 ወይም መሲሕ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።
35ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። 36የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም።
አይሁድ ባለማመን መጽናታቸው
37ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤ 38ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣
“ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ?
የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?”
ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።
39ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤
40“ዐይናቸውን አሳውሯል፤
ልባቸውንም አደንድኗል፤
ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤
በልባቸውም አያስተውሉም፤
እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።”
41ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ።
42ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር። 43ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው።
44ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤ 45እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። 46በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።
47 “ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና። 48በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም 49እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ። 50የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”
अहिले सेलेक्ट गरिएको:
ዮሐንስ 12: NASV
हाइलाइट
शेयर गर्नुहोस्
कपी गर्नुहोस्
तपाईंका हाइलाइटहरू तपाईंका सबै यन्त्रहरूमा सुरक्षित गर्न चाहनुहुन्छ? साइन अप वा साइन इन गर्नुहोस्
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.