ዘፍጥረት 2
2
1የሰማያትና የምድር፣ በውስጣቸውም ያሉት ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ።
2እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።#2፥2 ወይም አቆመ፤ በ3 ላይም እንዲሁ፤ 3እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና።
አዳምና ሔዋን
4 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት እንደዚህ ነበረ፤ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር 5የሜዳ ቡቃያ ገና በምድር#2፥5 ወይም መሬት፤ በ6 ላይም እንዲሁ ላይ አልታየም፤ የሜዳ ተክልም ገና አልበቀለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በመሬት ላይ ገና ዝናብ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚያለማ ሰው አልነበረም። 6ነገር ግን ውሃ#2፥6 ወይም ጭጋግ ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር። 7እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን#2፥7 በዕብራይስጥ ሰው (አዳም) የሚለው ቃል፣ ምድር (አዳማኽ) ከሚለው ቃል ጋር በድምፅ ይመሳሰላል፤ በፍቺም ሳይዛመድ አይቀርም፤ አዳም የመጀመሪያው ሰው ስምም ነው። ዘፍ 2፥20 ይመ አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።
8 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። 9እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ።
10የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። 11የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በሐዊላ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የፊሶን ወንዝ ነው። 12ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ#2፥12 ወይም መልካም ዕንቁ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። 13ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ#2፥13 ደቡብ ምሥራቅ መስጴጦምያ ሊሆን ይችላል። ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የግዮን ወንዝ ነው። 14ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተ ምሥራቅ የሚፈስሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።
15 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። 16እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። 17ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።”
18ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም)፣ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ።
19 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ። 20ስለዚህ አዳም#2፥20 ወይም ሰው ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው።
ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። 21እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንት#2፥21 ወይም ከሰው የጐን ክፍል ወስዶ ወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው። 22እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት#2፥22 ወይም ክፍል ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።
23አዳምም እንዲህ አለ፤
“እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣
ሥጋም ከሥጋዬ ናት።
ከወንድ ተገኝታለችና ሴት#2፥23 ሰው የሚል ትርጕም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ሴት የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። ትባል።”
24ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።
Trenutno izabrano:
ዘፍጥረት 2: NASV
Istaknuto
Podijeli
Kopiraj
Želiš li da tvoje istaknuto bude sačuvano na svim tvojim uređajima? Kreiraj nalog ili se prijavi
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.