ዘፍጥረት 9
9
እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር የገባው ኪዳን
1እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ 2አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል። 3ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።
4“ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። 5ሰውን የገደለ ሁሉ ስለ ሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።
6“የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ፣
ደሙ በሰው እጅ ይፈስሳል፤
በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አምሳል፣
እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሠርቶታልና።
7እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሰራፋ።”
8እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ 9“እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ 10እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንስሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ። 11ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።”
12እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ 13ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። 14ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ 15ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። 16ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን ዐስባለሁ።”
17ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።
የኖኅ ልጆች
18ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበሩ፤ ካም የከነዓን አባት ነው። 19ሦስቱ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከእነዚሁ ነው።
20ኖኅ ገበሬ ነበረና ወይን ተከለ፤#9፥20 ወይም የመጀመሪያ ነበር 21ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ ዕርቃኑን ተኛ። 22የከነዓን አባት ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ።
24ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ፣ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን ዐወቀ፤ 25እንዲህም አለ፤
“ከነዓን የተረገመ ይሁን፤
ለወንድሞቹም፣ የባሪያ ባሪያ ይሁን።”
26ደግሞም፤
“የሴም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይባረክ፤
ከነዓንም የሴም#9፥26 ወይም የእርሱ ባሪያ ይሁን ባሪያ ይሁን።
27እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የያፌትን#9፥27 ያፌት የሚለው ቃል መዘርጋት የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። ግዛት ያስፋ፤
ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤
ከነዓንም የእርሱ#9፥27 ወይም የእነርሱ ባሪያ ይሁን” አለ።
28ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ፤ 29ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖሮ ሞተ።
Nu markerat:
ዘፍጥረት 9: NASV
Märk
Dela
Kopiera
Vill du ha dina höjdpunkter sparade på alla dina enheter? Registrera dig eller logga in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.