የሉቃስ ወንጌል 24
24
ጌታ ስለ መነሣቱ
1ከሳምንቱም በመጀመሪያዪቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ። 2ያቺንም ድንጋይ ከመቃብሩ ላይ ተንከባልላ አገኙአት። 3ገብተውም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። 4ስለዚህም ነገር የሚሉትን አጥተው ሲያደንቁ ሁለት ሰዎች ከፊታቸው ቆመው ታዩአቸው፤ ልብሳቸውም ያብረቀርቅ ነበር። 5ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀረቀሩ። እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፥ “ሕያዉን ከሙታን ጋር ለምን ትሹታላችሁ? 6በዚህ የለም፤ ተነሥቶአል። በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንዲህ ሲል የተናገረውን ዐስቡ፦ 7#ማቴ. 16፥21፤ 17፥22-23፤ 20፥18-19፤ ማር. 8፥31፤ 9፥31። የሰው ልጅ በኀጢኣተኞች ሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” 10፥33-34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33። 8ቃሉንም ዐሰቡ። 9ከመቃብርም ተመልሰው ለዐሥራ አንዱና ለቀሩት ባልንጀሮቻቸው ሁሉ ይህን ነገር ነገሩአቸው። 10እነዚያም መግደላዊት ማርያም፥ ዮሐና፥ የያዕቆብ እናት ማርያም፥ አብረዋቸው የነበሩት ባልንጀሮቻቸውም ይህን ለሐዋርያት ነገሩአቸው። 11ይህም ነገር በፊታቸው እንደ ተረት መሰላቸውና አላመኑአቸውም። 12ጴጥሮስም ተነሣ፤ ወደ መቃብርም ፈጥኖ ሄደ፤ ዝቅ ብሎም በተመለከተ ጊዜ በፍታውን ለብቻው ተቀምጦ አየ፤ የሆነውንም እያደነቀ ተመለሰ።
በኤማሁስ መንገድ ስላገኙት ሰዎች
13በዚያም ቀን ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደምትርቀው ኤማሁስ ወደምትባለው መንደር ሄዱ። 14እርስ በርሳቸውም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ ይነጋገሩ ነበር። 15እነርሱም ይህን ሲነጋገሩና ሲመራመሩ ጌታችን ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ አብሮአቸውም ሄደ። 16እንዳያውቁትም ዐይናቸው ተይዞ ነበር። 17ጌታችንም፥ “በትካዜ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። 18ከእነርሱም ቀለዮጳ የሚባለው አንዱ መልሶ፥ “አንተ ብቻ ለኢየሩሳሌም እንግዳ ነህን? በእነዚህ ቀኖችስ በውስጥዋ የተደረገውን አታውቅምን?” አለው። 19ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህ ምንድነው?” አላቸው፤ እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “በእግዚአብሔር ፊትና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በቃሉና በሥራው ብርቱ ነቢይና እውነተኛ ሰው ስለነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፥ 20የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን አሳልፈው እንደ ሰጡት፥ ሞትም እንደ ፈረዱበትና እንደ ሰቀሉት ነው። 21እኛ ግን እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ እናደርግ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ይህ ነገር ከሆነ ዛሬ ሦስተኛ ቀን ነው። 22ደግሞም ሴቶች ከእኛ ዘንድ ወደ መቃብር ገስግሠው ሄደው ነበርና አስደንቀው ነገሩን። 23ሥጋውንም በአላገኙ ጊዜ ተመልሰው፦ ተነሥቶአል ያሉአቸውን የመላእክትን መልክ እንደ አዩ ነገሩን። 24ከእኛም ዘንድ ወደ መቃብር ሄደው እንዲሁ ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ ያገኙት አሉ፤ እርሱን ግን አላዩትም።” 25ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰነፎች፥ ነቢያትም የተናገሩትን ነገር ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ፥ 26ክርስቶስ እንዲህ ይሞት ዘንድ ወደ ክብሩም ይመለስ ዘንድ ያለው አይደለምን?” 27እርሱም ከሙሴና ከነቢያት፥ ከመጻሕፍትም ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን ይተረጕምላቸው ጀመር።
28ሊሄዱባት ወደ ነበረችው መንደርም ተቃረቡ፤ እርሱ ግን ይርቃቸው ጀመር። 29እነርሱም፥ “መሽቶአልና፥ ፀሐይም ተዘቅዝቆአልና፥ ከእኛ ጋር እደር” ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። 30ከዚህም በኋላ አብሮአቸው ለማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። 31ዐይናቸውም ተገለጠና ዐወቁት፤ ወዲያውኑም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እርስ በርሳቸውም እንዲህ አሉ፥ “በመንገድ ሲነግረን፥ መጻሕፍትንም ሲተረጕምልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?”
ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መመለሳቸው
33በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርትና አብረዋቸው የነበሩትንም ተሰብስበው አገኙአቸው፤ 34እንዲህ እያሉ፥ “ጌታችን በእውነት ተነሥቶአል፤ ለስምዖንም ታይቶታል።” 35እነርሱም በመንገድ የሆነውንና እንጀራውን ሲቈርስ ጌታችንን እንዴት እንዳወቁት ነገሩአቸው።
ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መገለጡ
36ይህንም ሲነጋገሩ ጌታችን ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አትፍሩ፤ እኔ ነኝ” አላቸው። 37እነርሱ ግን ፈሩ፤ ደነገጡም፤ ምትሐትንም የሚያዩ መሰላቸው። 38እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ምን ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ዐሳብ ለምን ይነሣሣል? 39እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደ ሆንሁም ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና።” 40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41ከድንጋጤ የተነሣም ገና ሳያምኑ ደስ ብሎአቸውም ሲያደንቁ ሳሉ፥ “በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። 42እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፤ ከማር ወለላም ጥቂት ሰጡት። 43ተቀብሎም በፊታቸው በላ፤ የተረፈውንም አንሥቶ ሰጣቸው።#“የተረፈውንም አንሥቶ ሰጣቸው” የሚለው በግሪኩ የለም።
44እርሱም፥ “በሙሴ ኦሪት፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ እንዳለው፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የነገርኋችሁ ነገሬ ይህ ነው” አላቸው። 45ከዚህም በኋላ መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። 46እንዲህም አላቸው፥ “ክርስቶስ እንዲሞት በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንዲነሣ፥ 47ንስሓና የኀጢኣት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ እንዲሁ ተጽፎአል። 48እናንተም ለዚህ ነገር ምስክሮች ናችሁ። 49#የሐዋ. 1፥4። እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ።”
ስለ ዕርገቱ
50እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው። 51#የሐዋ. 1፥9-11። እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለትና በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 53በቤተ መቅደስም ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያገለገሉ ኖሩ።
ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ወንጌላዊ ሉቃስ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ።
የጻፈውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በዐረገ በሃያ አንድ ዓመት ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አራት ዓመት በጽርዕ ቋንቋ ለመቄዶንያ ሰዎች ነው።
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። አሜን።
Kasalukuyang Napili:
የሉቃስ ወንጌል 24: አማ2000
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in