2
የሙሴ መወለድ
1በዚያን ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ። 2እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3ከዚያ በላይ ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ግን የደንገል ቅርጫት ወስዳ፣ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም በውስጡ አስተኝታ ቅርጫቱን አባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው። 4የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ታይ ነበር።
5በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች፤ በምትታጠብበትም ጊዜ ደንገጥሮቿ በወንዙ ዳር ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር፤ በቄጠማውም መካከል የተቀመጠ ቅርጫት አይታ ከደንገጥሮቿ አንዷን እንድታመጣው ላከቻት። 6ቅርጫቱን ስትከፍተው ሕፃኑን በውስጡ አየች፤ ያለቅስ ስለ ነበርም ዐዘነችለትና፣ “ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ መሆን አለበት” አለች።
7የሕፃኑ እኅት ለፈርዖን ልጅ፣ “ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽን?” አለቻት።
8የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጂቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች። 9የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው። 10ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ#2፥10 በዕብራይስጥ ሙሴ የሚለው የቃል ድምፅ፣ ማውጣት ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። ብላ ጠራችው።
ሙሴ ወደ ምድያም ምድር ሸሸ
11ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብፃዊ ሲደበድበው አየ። 12ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብፃዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው። 13በማግስቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው።
14ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቋል!” በማለት ፈራ።
15ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። 16የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጕድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት። 17እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።
18ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሯችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው።
19እነርሱም፣ “አንድ ግብፃዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት።
20አባታቸውም፣ “ሴቶች ልጆቹን የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና አብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው።
21ሙሴም ከሰውየው ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ራጉኤልም ልጁን ሲፓራን ዳረለት። 22ሲፓራም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ሲል የልጁን ስም ጌርሳም#2፥22 በዕብራይስጥ ጌርሳም የሚለው ቃል ድምፅ፣ መጻተኛ በዚያ አለ ከሚለው ሐረግ ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። ብሎ ጠራው።
23ከብዙ ዓመት በኋላ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙትም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ደረሰ። 24እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ፤ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን ዐሰበ። 25እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እስራኤላውያንን ተመለከተ፤ ስለ እነርሱም ገደደው።