Logo ng YouVersion
Hanapin ang Icon

ዘፍጥረት 19

19
ሰዶምና ገሞራ ጠፉ
1ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግምባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው። 2እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ ዐድራችሁም ጧት በማለዳ ጕዟችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው።
እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት።
3ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ። 4ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከየአካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት። 5ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት።
6ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተ ኋላው ዘግቶ፣ 7እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ። 8እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።”
9እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰድዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳናደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ።
10ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ። 11ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ።
12ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤ 13ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።”
14ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች#19፥14 ወይም ሴት ልጆቹን ያገቡትን የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው።
15ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት።
16ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው። 17እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው።
18ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤#19፥18 ወይም እንደዚህስ አይሁን ጌታ፤ ወይም እንደዚህስ አይሁን ጌታዬ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤ 19እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደ ሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል። 20እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።”
21እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም። 22አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር#19፥22 ዞዓር ማለት ትንሽ ማለት ነው። ተባለ።
23ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። 24ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው። 25እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው። 26የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች።
27አብርሃም በማግስቱም፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሄደ። 28ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቍልቍል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ።
29እንደዚህ አድርጎ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን ዐሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።
ሎጥና ሴት ልጆቹ
30ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ አደረገ። 31አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቷል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ አብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም። 32ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።”
33በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።
34በማግስቱም ታላቂቱ ልጅ ታናሺቱን፣ “እኔ ትናንትና ማታ ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ፤ ዛሬም እንደ ገና የወይን ጠጅ እናጠጣው፤ አንቺም ደግሞ ከእርሱ ዘንድ ገብተሽ ተኚ፤ በዚህም የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ከአባታችን ዘር ማትረፍ እንችላለን” አለቻት። 35በዚያችም ምሽት ደግሞ አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ትንሿ ልጁም ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።
36ስለዚህ ሁለቱም የሎጥ ሴት ልጆች ከአባታቸው አረገዙ። 37ትልቋ ልጁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ ሞዓባውያን#19፥37 ሞዓብ የሚለው ቃል ከአባት የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። አባት ነው። 38ትንሿ ልጁም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ#19፥38 ቤንአሚ ማለት የሕዝቤ ልጅ ማለት ነው። ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ አሞናውያን አባት ነው።

Kasalukuyang Napili:

ዘፍጥረት 19: NASV

Haylayt

Ibahagi

Kopyahin

None

Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in