26
ይስሐቅና አቢሜሌክ
26፥1-11 ተጓ ምብ – ዘፍ 12፥10-20፤ 20፥1-18
1ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከደረሰው ራብ ሌላ፣ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። ይስሐቅም የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ ወደሚኖርበት ወደ ጌራራ ሄደ። 2በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለይስሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብፅ አትውረድ፤ 3ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ። 4ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። 5ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።” 6ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ተቀመጠ።
7የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለ ሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በእርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር።
8ይስሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይስሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። 9አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት እኅቴ ናት ትላለህ?” አለው።
ይስሐቅም፣ “በእርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። 10አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው።
11አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ።
12ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። 13ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። 14ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። 15ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሯቸውን የውሃ ጕድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኗቸው።
16አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው።
17ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። 18ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኗቸውን የውሃ ጕድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው።
19የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጕድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ።
20የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይስሐቅ ያን የውሃ ጕድጓድ ኤሴቅ#26፥20 ኤሴቅ ማለት ክርክር ማለት ነው። ብሎ ጠራው፤ በጕድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። 21አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጕድጓዱን ስጥና#26፥21 ስጥና ማለት ተቃውሞ ማለት ነው። ብሎ ጠራው። 22ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጕድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጕድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት#26፥22 ርኆቦት ማለት ክፍል (የቤት) ማለት ነው። ብሎ ጠራው።
23ከዚያም ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። 24በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።
25ይስሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ።
26አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ከጌራራ ተነሥቶ ይስሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ። 27ይስሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።
28እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካከል የሚጸና ውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋር ስምምነት እናድርግ፤ 29አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባርኮሃል።” 30ይስሐቅም ድግስ ደግሶ አበላቸው፤ አጠጣቸው። 31በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ።
32በዚያኑ ዕለት፣ የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጕድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት። 33እርሱም የውሃውን ጕድጓድ ሳቤህ#26፥33 ሳቤህ ማለት መሐላ ወይም ሰባት ማለት ሊሆን ይችላል። አለው፤ ከዚያም የተነሣ የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ ይጠራል።
34ዔሳው አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ የኬጢያዊውን የብኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የኬጢያዊውን የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትን አገባ፤ 35በእነዚህም ሴቶች ምክንያት የይስሐቅና የርብቃ ልብ ያዝን ነበር።