Logo ng YouVersion
Hanapin ang Icon

ዘፍጥረት 33

33
የያዕቆብና የዔሳው መገናኘት
1ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ልጆቹን ለልያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮች አከፋፈላቸው። 2ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ። 3እርሱ ራሱም ቀድሟቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።
4ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው።
ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው።
6በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤ 7ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ።
8ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድን ነው?” አለው።
እርሱም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።
9ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው” አለው።
10ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት እንደ ማየት እቈጥረዋለሁ። 11እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብሁልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ።
12ዔሳውም “በል ተነሥና ጕዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው።
13ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ። 14ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጕዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።”
15ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው።
ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ ጌታዬ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው።
16ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ። 17ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት#33፥17 ሱኮት ማለት መጠለያዎች ማለት ነው። ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ።
18ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ በከነዓን ወዳለችው ወደ ሴኬም በደኅና ደረሰ፤#33፥18 ወይም ሳሌም ደረሰ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። 19ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ ከኤሞር ልጆች በመቶ ጥሬ ብር ገዛ፤ ኤሞርም የሴኬም አባት ነበር። 20በዚያም መሠዊያ አቁሞ፣ ኤል ኤሎሄ እስራኤል#33፥20 ኤል ኤሎሄ እስራኤል ማለት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ወይም የእስራኤል አምላክ ኀያል ነው ማለት ነው። ብሎ ጠራው።

Kasalukuyang Napili:

ዘፍጥረት 33: NASV

Haylayt

Ibahagi

Kopyahin

None

Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in