39
ዮሴፍና የጲጥፋራ ሚስት
1በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው።
2 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። 3አሳዳሪውም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ 4ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። 5ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) የግብፃዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። 6ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፣ ማናቸውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር።
ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ 7እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፣ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው።
8እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። 9በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” 10ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛት ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም።
11አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። 12እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።
13እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ 14የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ 15ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።”
16ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቈየችው። 17ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ 18ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”
19ጌታውም፣ “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ ተቈጣ። 20ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው።
21ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፤ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። 22ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። 23እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፣ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ጕዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር።