50
1ዮሴፍ በአባቱ ፊት ተደፍቶ አለቀሰ፤ ሳመውም። 2ከዚያም የአባቱ የእስራኤል ሬሳ እንዳይፈርስ ባለ መድኀኒት የሆኑ አገልጋዮቹ በመድኀኒት እንዲቀቡት አዘዘ። ባለ መድኀኒቶቹም እንዳይፈርስ ሬሳውን በመድኀኒት ቀቡት። 3ሬሳው እንዳይፈርስ መድኀኒት መቀባቱ በአገሩ ልማድ መሠረት አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ግብፃውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት።
4የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩልኝ፤ 5‘የምሞትበት ጊዜ ስለ ተቃረበ፣ በከነዓን ምድር ራሴ ቈፍሬ በአዘጋጀሁት መቃብር እንድትቀብረኝ’ ሲል አባቴ አስምሎኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ልቅበር፤ ከዚያም እመለሳለሁ።”
6ፈርዖንም፣ “በአስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው።
7ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንዲሁም የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት። 8እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ አብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ። 9እንዲሁም ሠረገሎችና ፈረሰኞች#50፥9 ወይም ሠረገለኞች አብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበረ።
10እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ልቅሶ ተቀመጠ። 11በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብፃውያን መራራ ልቅሷቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል#50፥11 አቤል ምጽራይም ማለት የግብፃውያን ሐዘን ማለት ነው። ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር።
12የያዕቆብ ልጆችም አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ 13አስከሬኑን ወደ ከነዓን ምድር ወስደው አብርሃም ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ላይ ከነዕርሻው በገዛው፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት።
14ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ፣ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር አብረውት ሄደው ከነበሩት ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ተመለሰ።
ዮሴፍ ወንድሞቹን እንደማይበቀላቸው አረጋገጠ
15የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። 16ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ 17‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም፣ የእኛን የአባትህን አምላክ (ኤሎሂም) አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ።
18ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት።
19ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቦታ ማን አስቀመጠኝ? 20እናንተ እኔን ለመጕዳት ዐስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። 21አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦ፣ በደግ ቃል አናገራቸው።
የዮሴፍ መሞት
22ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋር በግብፅ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤ 23የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ። የምናሴ ልጅ ማኪር የወለዳቸውም ልጆች በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።
24ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን፣ “እነሆ፤ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቧል፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በረድኤቱ ይጐበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባችኋል” አላቸው። 25ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያን ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” ሲል አስማላቸው።
26ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ፤ ሬሳው እንዳይፈርስ በአገሩ ደንብ በመድኀኒት ከደረቀ በኋላ፣ ሣጥን ውስጥ አስገብተው በግብፅ ምድር አስቀመጡት።