Logo ng YouVersion
Hanapin ang Icon

ሉቃስ 15

15
የጠፋው በግ ምሳሌ
15፥4-7 ተጓ ምብ – ማቴ 18፥12-14
1አንድ ቀን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ኀጢአተኞች” ሁሉ ሊሰሙት በዙሪያው ተሰበሰቡ። 2ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጕረመረሙ።
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ 4“ከእናንተ መካከል አንዱ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ላይ ጥሎ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው? 5ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ተሸክሞ፣ 6ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹንም በአንድነት ጠርቶ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል። 7እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።
የጠፋው ሳንቲም ምሳሌ
8 “ወይም ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋባት፣ እስክታገኘው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷን ጠርጋ፣ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? 9ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጎረቤቶቿን በአንድነት ጠርታ፣ ‘የጠፋብኝን የብር ሳንቲም አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች። 10እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።”
ጠፍቶ የተገኘው ልጅ ምሳሌነት
11ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።
13 “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ። 14እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር። 15ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው። 16ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም።
17 “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ 18ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ 19ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’ 20ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ።
“ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው።
21 “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው። # 15፥21 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንኳ እንደ አንዱ ቈጥረህ ተቀበለኝ የሚል አላቸው።
22 “አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤ 23የሠባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤ 24ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቷል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።
25 “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ 26እርሱም ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደ ሆነ ጠየቀው። 27አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሠባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው።
28 “ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው። 29እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤ 30ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሠባውን ፍሪዳ ዐረድህለት።’
31 “አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ 32ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሓ ልናደርግ ይገባናል።’ ”

Kasalukuyang Napili:

ሉቃስ 15: NASV

Haylayt

Ibahagi

Kopyahin

None

Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in