ኦሪት ዘፍጥረት 20
20
አብርሃምና አቤሜሌክ
1አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር አቅጣጫ ሄደ፤ በቃዴስና በሱር መካከልም ኖረ፤ በጌራራም በእንግድነት ተቀመጠ። 2አብርሃምም ሚስቱን ሣራን “እኅቴ ናት” አላቸው፤ የከተማዪቱ ሰዎች ስለ እርስዋ እንዳይገድሉት “ሚስቴ” ናት ማለትን ፈርቶአልና፤ የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክም ላከና ሣራን ወሰዳት። 3በዚያች ሌሊትም አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር በሕልም ወደ እርሱ መጣ፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ትሞታለህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና።” 4አቤሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፤ አቤሜሌክም እንዲህ አለ፥ “አቤቱ ያላወቀውን ሕዝብ በእውነት ታጠፋለህን? 5እኅቴ ናት ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርስዋ ደግሞ ራስዋ ወንድሜ ነው አለች፤ በልቤ ቅንነትና በእጄ ንጹሕነት ይህን አደረግሁት።” 6እግዚአብሔርም በሕልም አለው፥ “ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ ዐወቅሁ፤ እኔም ደግሞ በፊቴ ኀጢአትን እንዳትሠራ ጠበቅሁህ፤ ስለዚህም ትቀርባት ዘንድ አልተውሁህም። 7አሁንም የሰውየውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፤ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት፥ ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በርግጥ ዕወቅ።” 8አቤሜሌክም በጥዋት ተነሣ፤ ብላቴኖቹንም ሁሉ ጠራ፤ ይህንም ነገር ሁሉ በጆሮአቸው ተናገረ፤ ቤተ ሰዎቹም ሁሉ እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ። 9አቤሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው፥ “ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኀጢአት አውርደሃልና፤ ማንም የማያደርገው የማይገባ ሥራ በእኔ ሠራህብኝ።” 10አቤሜሌክም አብርሃምን አለው፥ “ይህን ነገር ማድረግህ ምን አይተህ ነው?” 11አብርሃምም አለ፥ “ምንአልባት በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት ስለሌለ በሚስቴ ምክንያት ይገድሉኛል ብዬ ነው። 12እርስዋም ደግሞ በእናቴ ወገን አይደለችም እንጂ በእውነት በአባቴ ወገን እኅቴ ናት፤ ለእኔም ሚስት ሆነች። 13እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት፥ ‘ይህን ጽድቅ አድርጊልኝ፤ በገባንበት ሀገር ሁሉ ወንድሜ ነው በዪ።’ ” 14አቤሜሌክም አንድ ሺህ ምዝምዝ ብርን#“አንድ ሺህ ምዝምዝ ብርን” የሚለው በዕብ. የለም። በጎችንና ላሞችን፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን አመጣ፤ ለአብርሃምም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15አቤሜሌክም አብርሃምን አለው፥ “እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፤ በወደድኸው ተቀመጥ።” 16ሣራንም አላት “እነሆ፥ ለወንድምሽ አንድ ሺህ ምዝምዝ ብር ሰጠሁት፤ ይህም ለፊትሽ ክብር ይሁንሽ፤ በሁሉም እውነትን ተናገራት።” 17አብርሃምም ወደ እግዚዘብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቤሜሌክን፥ ሚስቱንም፥ ሴቶች ልጆቹንም፥ በቤቱ ውስጥ ያሉ ሴቶች አገልጋዮቹንም ፈወሳቸው፤ እነርሱም ወለዱ፤ 18እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቤሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና።
Поточний вибір:
ኦሪት ዘፍጥረት 20: አማ2000
Позначайте
Поділитись
Копіювати
Хочете, щоб ваші позначення зберігалися на всіх ваших пристроях? Зареєструйтеся або увійдіть