ኦሪት ዘፍጥረት 23
23
የሣራ መሞትና አብርሃም የመቃብር ቦታ መግዛቱ
1የሣራም ዕድሜ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሆነ። 2ሣራም በቈላ ውስጥ ባለች አርባቅ በምትባል ከተማ ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ። 3አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፤ ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 4“እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ እንድገዛ የመቃብር ርስት ስጡኝ፤ ሬሳዬንም እንደ እናንተ ልቅበር።” 5የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፤ አሉትም፦ 6“አይሆንም፥ ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእኛ ንጉሥ ነህና ከመቃብር ስፍራችን በመረጥኸው ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን በዚያ ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።” 7አብርሃምም ተነሣ፤ በሀገሩ ሕዝብ ፊትም ለኬጢ ልጆች ሰገደ። 8እንዲህም አላቸው፥ “ሬሳዬን ከፊቴ አርቄ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፤ ለሰዓር ልጅ ለኤፍሮንም ስለ እኔ ንገሩት፤ 9በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን ይስጠኝ፤ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን በሚገባው ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፤ ከእርሱም እገዛለሁ።” 10ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ 11“አይደለም፥ ጌታዬ፥ ቀርበህ ስማኝ፤ እርሻውን፥ በውስጡም ያለውን ዋሻውን ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።” 12አብርሃምም በሀገሩ ሕዝብ ሁሉ ፊት ሰገደ፤ 13የሀገሩ ሕዝብም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ከእኔ ቅርብ ነህና ስማኝ፤ የእርሻህንም ዋጋ ከእኔ ውሰድ፤ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።” 14ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “አይሆንም፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ 15የአራት መቶ ምዝምዝ ብር ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካከል ምንድን ነው? እንግዲህ ሬሳህን በዚያ ቅበር።” 16አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውንና ተቀባይነት ያለውን ግብዝ ያይደለ አራት መቶ ምዝምዝ ብር መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው።
17በመምሬ ፊት ያለው ባለ ድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻም ለአብርሃም ጸና፤ እርሻው፥ በእርሱም ያለ ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው ዕንጨት ሁሉ፤ 18በኬጢ ልጆችና በከተማዪቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ። 19ከዚህም በኋላ አብርሃም ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ሚስቱን ሣራን ቀበረ። 20እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻም በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።#ምዕ. 23 ቍ. 20 ላይ የሚነበበው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. ብቻ ያለ ነው።
Поточний вибір:
ኦሪት ዘፍጥረት 23: አማ2000
Позначайте
Поділитись
Копіювати
Хочете, щоб ваші позначення зберігалися на всіх ваших пристроях? Зареєструйтеся або увійдіть