ኦሪት ዘፍጥረት 16

16
1የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት 2ሦራም አብራምን፤ እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋግባ አለችው፤ 3አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኍላ፤ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። 4እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። 5ሦራም አብራምን፥ መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ፥ መካከል ይፍረስ አለችው። 6አብራምም ሦራን፥ እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦርም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች።
7የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። 8እርሱም፤ የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም፥ እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች። 9የእግዚአብሔር መልአክም፥ ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት። 10የእግዚአብሔር መልአክም፥ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት። 11የእግዚአብሔር መልአክም አላት፥ እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና። 12እርሱም የበዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል። 13እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። 14ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው።
15አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው። 16አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ።

Kleurmerk

Deel

Kopieer

None

Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan