1 ዜና መዋዕል 17

17
እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ተስፋ
17፥1-15 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥1-17
1ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በተቀመጠበት ጊዜ፣ ነቢዩ ናታንን “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።
2ናታንም ለዳዊት፣ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት።
3በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤
4“ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም። 5እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። 6በእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ባለፍሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው#17፥6 በዚህና በቍጥር 10 ላይ በትውፊት፣ መሳፍንት ይባላል “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁት አለን?’
7“አሁንም ባሪያዬ ዳዊትን እንዲህ በለው፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ። 8በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ። 9የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህ በኋላም እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጣቸዋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ክፉዎች ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤ 10ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ።
“ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤ 11ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ፤ 12ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ። 13አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንዳራቅሁ ሁሉ፣ ከርሱ ላይ ከቶ አልወስድም። 14በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።’ ”
15ናታንም የዚህን ራእይ ቃል በሙሉ ለዳዊት ነገረው።
የዳዊት ጸሎት
17፥16-27 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥18-29
16ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 17አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።
18“ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህ፤ 19እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።
20“አቤቱ፤ እግዚአብሔር እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21ከግብጽ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ። 22ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።
23እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ 24ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።
25“አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ። 26አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል። 27በፊትህ ለዘላለም እንዲኖር አሁንም የባሪያህን ቤት ልትባርክ ወድደሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የባረክኸው አንተ ስለ ሆንህ፣ ለዘላለም የተባረከ ይሆናል።”

ማድመቅ

ኮፒ

አወዳድር

ያጋሩ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ