1 ቆሮንቶስ 5
5
አሳፋሪ ኀጢአት በቤተ ክርስቲያን
1በመካከላችሁ የዝሙት ርኩሰት እንዳለ በርግጥ ይወራል፤ እንዲህ ያለው ርኩሰት በአረማውያን ዘንድ እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ነው፤ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው አለና። 2ደግሞም ታብያችኋል! ይልቅስ ሐዘን ተሰምቷችሁ፣ ይህን ድርጊት የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ልታስወግዱት አይገባምን? 3ምንም እንኳ እኔ በአካል አብሬያችሁ ባልሆንም፣ በመንፈስ ግን ከእናንተ ጋራ ነኝ፤ ልክ አብሬያችሁ እንዳለሁ ሆኜ፣ ይህን ባደረገው ሰው ላይ አሁኑኑ ፈርጄበታለሁ። 4በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በመንፈስ ከእናንተ ጋራ ስለምሆን፣ በጌታችን በኢየሱስ ስምና በመካከላችሁ በሚገኘው በጌታችን በኢየሱስ ኀይል፣ 5ሥጋው#5፥5 ወይም ኀጢአተኛ ተፈጥሮው ወይም አካሉ ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ።
6መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁምን? 7አሁን ያለ እርሾ እንደ ሆናችሁ ሁሉ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቷልና። 8ስለዚህ በዓሉን ግፍና ክፋት በሞላበት እርሾ፣ በአሮጌ እርሾ ሳይሆን፣ እርሾ በሌለበት ቂጣ በቅንነትና በእውነት እናክብር።
9ከሴሰኞች ጋራ እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጽፌላችሁ ነበር፤ 10እንዲህም ስል በጠቅላላው ከዚህ ዓለም ሴሰኞች ወይም ስግብግቦችና ቀማኞች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋራ አትተባበሩ ለማለት አይደለም፤ እንደዚያማ ቢሆን ከዚህ ዓለም ጨርሶ መለየት ያስፈልጋችሁ ነበር። 11ነገር ግን አሁን የጻፍሁላችሁ፣ “ወንድም ነኝ”#5፥11 በግሪኩ አዴልፎስ የሚለው ቃል ወንድ የሆኑ የክርስቶስ ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም የሚያጠቃልል ነው። እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋራ እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋራ ምግብ እንኳ አትብሉ።
12ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔን ምን አግብቶኝ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? 13ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ላይ የሚፈርድ ግን እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ፣ “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።”#5፥13 ዘዳ 13፥5፤ 17፥7፤ 19፥19፤ 21፥21፤ 22፥21-24፤ 24፥7
Currently Selected:
1 ቆሮንቶስ 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.