1 ነገሥት 15
15
የይሁዳ ንጉሥ አብያ
15፥1-2፤ 15፥7-8 ተጓ ምብ – 2ዜና 13፥1-2፤ 13፥22–14፥1
1የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ#15፥1 በዚህ ስፍራና በ7 እና 8 ላይ እንዳንድ የዕብራይስጥና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ (በተጨማሪም 2ዜና 12፥16 ይመ)፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን፤ አቢያም ይላሉ። በይሁዳ ነገሠ፤ 2በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
3እርሱም አባቱ ከርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም። 4ነገር ግን ከርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው። 5ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።
6አብያም#15፥6 አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ አንዳንድ የዕብራይስጥና የሱርስት ትርጕሞች ግን፣ አቢጃም ይላሉ። በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር። 7ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር። 8አብያም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በርሱ ፈንታ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሳ
15፥9-22 ተጓ ምብ – 2ዜና 14፥2-3፤ 15፥16–16፥6
15፥23-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 16፥11–17፥1
9የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 10በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
11አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ። 12የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ። 13አሳም ለአስጸያፊዋ የአሼራ ጣዖት ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። 14አሳ የማምለኪያ ኰረብቶችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር ፍጹም ነበር። 15እርሱና አባቱ የቀደሱትን ብር፣ ወርቅና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስገባ።
16አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር። 17የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።
18አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በሹማምቱ እጅ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሃዳድ ላከ። 19“ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑር። እነሆ፤ የብርና ወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋራ ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው።
20ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እርሱም ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ኪኔሬትን በሙሉ ድል አድርጎ ያዘ። 21ባኦስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን መገንባቱን አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ። 22ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ ሲሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ በእነርሱም ንጉሡ አሳ የብንያምን ጌባዕና ምጽጳን ሠራበት።
23በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ጀግንነቱ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹን ታመመ። 24አሳ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በርሱ ፈንታ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ
25በይሁዳ ንጉሥ በአሳ ዘመነ መንግሥት በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። 26እርሱም በአባቱ መንገድ በመሄድ፣ አባቱ የሠራውንና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመሥራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።
27ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከብበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው። 28ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው።
29ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤ 30ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ በማነሣሣቱ ነው።
31ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 32አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።
የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ
33የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ። 34በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 15: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.