1 ነገሥት 22
22
ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ
22፥1-28 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥1-27
1በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም። 2በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ። 3የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።
4ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ላይ ለመዝመት ዐብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው።
ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው። 5ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።
6ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ልዝመት ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።
7ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።
8የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ምን ጊዜም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ።
ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።
9ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።
10የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ መግቢያ በር አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 11በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።
12የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው።
14ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ።
15ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም፣ “ሂዱና ድል አድርጉ እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት።
16ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።
17ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ።
18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።
19ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 20እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።
“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ። 21ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።
22“እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።
“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና፤ በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።
“እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ’ አለው።
23“ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል።”
24ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።
25ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።
26ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ 27ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ።
28ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።
አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው በሬማት ተገደለ
22፥29-36 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥28-34
29ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ። 30የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።
31በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር፤ 32የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ 33የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ዐውቀው መከታተሉን ተዉት።
34ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው። 35ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቍስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ። 36ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ።
37ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ። 38ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ#22፥38 ወይም፣ የጦር መሣሪያ በሚታጠብበት በሰማርያ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። ኵሬ ዐጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት።
39ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝኆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? 40አክዓብም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ
22፥41-50 ተጓ ምብ – 2ዜና 20፥31–21፥1
41የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ። 42ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዐምስት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሃያ ዐምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። 43እርሱም በአካሄዱ ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። 44እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋራ በሰላም ኖረ።
45የቀረውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያከናወናቸው ተግባራት፦ ጀግንነቱና ያደረጋቸው ጦርነቶች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይሉምን? 46ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ። 47በዚያ ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።
48ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የተርሴስ#22፥48 ሰብዓ ሊቃናት የንግድ መርከቦች ይላል። መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር። 49በዚያ ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋራ በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ዕሺ አላለውም።
50ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በምትኩ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ
51የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ። 52እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ። 53አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲነሣሣ አደረገ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 22: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.