1 ነገሥት 8
8
ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ
8፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 5፥2–6፥11
1ከዚያም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ፣ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 2በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ።
3የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜ፣ ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤ 4የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተሸከሟቸው። 5ንጉሥ ሰሎሞንና ዐብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ በታቦቱ ፊት ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች ሠዉ።
6ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። 7ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። 8መሎጊያዎቹ በጣም ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከቅድስት ይታዩ ነበር፤ ከቅድስት ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 9እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
10ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው። 11የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም።
12ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ 13እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።”
14መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። 15ከዚያም እንዲህ አለ፤
“ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ 16‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’
17“አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ 18እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ ማሰብህ መልካም አድርገሃል፤ 19ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’
20“እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሟል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። 21ከግብጽ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋራ የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”
ሰሎሞን በምረቃው ላይ ያቀረበው ጸሎት
8፥22-53 ተጓ ምብ – 2ዜና 6፥12-40
22ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣ 23እንዲህም አለ፤
“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋራ የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤ 24ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።
25“አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ በጥንቃቄ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። 26እንግዲህ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።
27“ነገር ግን አምላክ በርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! 28ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። 29ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወደ አልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ። 30ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
31“አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ 32ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት።
33“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣ 34በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።
35“አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ 36በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸውም ምድርህ ላይ ዝናብን አዝንብ።
37“በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር፣ ዋግ ወይም አረማሞ፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚከሠትበት ጊዜ፣ ወይም ከተሞቻቸውን ጠላት በሚከብብበት ጊዜ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ 38ከሕዝብህ ማንኛውም ሰው ወይም መላው እስራኤል የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ማንኛውንም ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ 39በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤ 40ይኸውም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩህ ነው።
41“ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ነገር ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ ባዕድ ሰው ቢኖር፣ 42ሰዎች ከሩቅ የመጣው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምቶ ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣ 43አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።
44“ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ፣ 45ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ፍትሕንም አጐናጽፋቸው።
46“መቼም ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ እነርሱም ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ የጠላት ምድር ቢጋዙ፣ 47በተጋዙበት አገር ሳሉ ወደ ልቡናቸው ቢመለሱ፣ ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ምድር ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ 48እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸው አገር፣ በምርኮ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ ወደ መረጥሃትም ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣ 49በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና፤ ልመናቸውን ስማ፤ ፍረድላቸውም። 50በአንተ ላይ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ። 51ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና።
52“አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ 53ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”
54ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ። 55ከዚያም ቆሞ መላውን የእስራኤልን ጉባኤ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ ሲል መረቀ፤
56“በሰጠው ተስፋ መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን ለሰጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ በባሪያው በሙሴ አማካይነት ከተሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ አንድም ቃል አልቀረምና። 57አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋራ እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛም ጋራ ይሁን፤ አይተወን፤ አይጣለንም። 58በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ። 59በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ። 60ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደ ሆነና ከርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው። 61ስለዚህ እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ፣ በሥርዐቱ እንድትኖሩና ትእዛዙን እንድትጠብቁ ልባችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተገዛ ይሁን።”
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
8፥62-66 ተጓ ምብ – 2ዜና 7፥1-10
62ከዚያም ንጉሡና ከርሱ ጋራ ያሉት እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። 63ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺሕ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺሕ በግና ፍየል የኅብረት መሥዋዕት#8፥63 በዚህና በ64 ላይ በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት ይባላል። አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ንጉሡና እስራኤላውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ።
64በዚያ ዕለትም ንጉሡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከለኛ ክፍል ቀደሰ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ አቀረበ፤ ይህን ያደረገውም በእግዚአብሔር ፊት የነበረው የናስ መሠዊያ በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሣ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት የእህሉን ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ መያዝ ባለመቻሉ ነበር።
65በዚያ ጊዜም ሰሎሞን ዐብረውት ከነበሩት ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋራ፣ ማለትም ከሐማት መተላለፊያ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝ#8፥65 ወይም ከመግቢያው ጀምሮ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ካለው ምድር ከተሰበሰበው ታላቅ ጉባኤ ጋራ በዓሉን አከበረ። እነርሱም ሰባት ቀን፣ በተጨማሪም ሌላ ሰባት ቀን በድምሩ ዐሥራ አራት ቀን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በዓሉን አከበሩ። 66በስምንተኛው ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም ንጉሡን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት በማድረግ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 8: NASV
ማድመቅ
ያጋሩ
አወዳድር
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.