2 ተሰሎንቄ 2
2
የዐመፅ ሰው
1ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱም ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ 2በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደ ተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሷል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሯችሁ አትናወጡ፤ አትደንግጡም። 3ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታልላችሁ፤ አስቀድሞ ዐመፅ ሳይነሣ፣ ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ#2፥3 አንዳንድ ቅጆች የኀጢአት ይላሉ። ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። 4እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል።
5ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበር ትዝ አይላችሁምን? 6በራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን ምን እንደሚከለክለው ታውቃላችሁ። 7የዐመፅ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሠራ ነውና፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የሚከለክለው ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው። 8ከዚያም በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ የሚያጠፋው ዐመፀኛ ይገለጣል። 9የእርሱም አመጣጥ እንደ ሰይጣን አሠራር ሲሆን፣ ይህም በኀይል ሁሉ፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆችም ሁሉ ይሆናል፤ 10እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን ባለመውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል። 11በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በሐሰት እንዲያምኑ የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፤ 12ይህም የሚሆነው እውነትን ያላመኑት ነገር ግን በክፋት ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።
ጸንታችሁ ቁሙ
13በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር እናንተን ከመጀመሪያ አንሥቶ በመንፈስ ተቀድሳችሁና በእውነትም አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል።#2፥13 አንዳንድ ቅጆች እግዚአብሔር በኵራቱ እንድትሆኑ መርጧችኋል ይላሉ። 14የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ተካፋዮች እንድትሆኑም በወንጌላችን አማካይነት ጠርቷችኋል።
15እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በአንደበታችንም ሆነ በመልእክታችን ያስተላለፍንላችሁን ትምህርት#2፥15 ወይም ወግ አጥብቃችሁ ያዙ።
16ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደግሞም እኛን የወደደንና በጸጋው የዘላለም መጽናናትና መልካም ተስፋን የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን፣ 17ልባችሁን ያጽናኑት፤ በበጎ ሥራና በቃል ሁሉ ያበርቷችሁ።
Currently Selected:
2 ተሰሎንቄ 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.