የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 16

16
ጢሞቴዎስ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋራ ተሰማራ
1ጳውሎስ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ደረሰ። በዚያም እናቱ አይሁዳዊት ሆና በጌታ ያመነች፣ አባቱ ግን የግሪክ ሰው የሆነ፣ ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። 2እርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው። 3ጳውሎስም ይህ ሰው ከርሱ ጋራ እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ አባት የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና። 4እነርሱም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን ውሳኔ ተቀብለው እንዲጠብቁ ለምእመናኑ ይሰጡ ነበር። 5አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር።
ጳውሎስ ስለ መቄዶንያው ሰው ያየው ራእይ
6ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ። 7ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታንያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። 8ስለዚህ በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። 9ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። 10ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።
ልድያ በፊልጵስዩስ በጌታ አመነች
11ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጕዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጕዟችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤ 12ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን።
13በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን። 14ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ ልቧን ከፈተላት። 15እርሷና ቤተ ሰዎቿ ከተጠመቁ በኋላም፣ “በጌታ ማመኔን በርግጥ ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ጥቂት ተቀመጡ” በማለት አጥብቃ ለመነችን።
ጳውሎስና ሲላስ በወህኒ ቤት
16አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። 17ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር ባሮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤ 18ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት።
19አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። 20ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ 21ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም ያልተፈቀደልንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።”
22ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። 23ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። 24እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋራ አጣብቆ አሰራቸው።
25እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። 26ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። 27የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። 28ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኛ ሁላችን እዚሁ ስላለን፣ በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርስ!” ብሎ ጮኸ።
29የወህኒ ቤቱ ጠባቂም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ዘልሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ላይ ወደቀ። 30ይዟቸው ከወጣ በኋላ፣ “ጌቶች ሆይ፤ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው።
31እነርሱም፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” አሉት። 32ከዚያም ለርሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩ። 33የወህኒ ቤት ጠባቂውም ሌሊት በዚያ ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን ዐጠበላቸው፤ ወዲያውም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ። 34የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ወደ ቤቱ ወስዶ ማእድ አቀረበላቸው፤ ከቤተ ሰቡም ሁሉ ጋራ በእግዚአብሔር በማመኑ በደስታ ተሞላ።
35ሲነጋም፣ ገዦቹ፣ “እነዚያን ሰዎች ፈተህ ልቀቃቸው” ብለው መኰንኖቻቸውን ላኩበት። 36የወህኒ ቤት ጠባቂውም፣ “ገዦቹ እንድትፈቱ አዝዘዋል፤ ስለዚህ ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ” ብሎ ለጳውሎስ ነገረው።
37ጳውሎስ ግን፣ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለን፣ በሕዝብ ፊት ያለ ፍርድ ደብድበው ወደ እስር ቤት ወረወሩን፤ ታዲያ አሁን በስውር ሊያስወጡን ይፈልጋሉ? ይህማ አይሆንም፤ እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን!” አላቸው።
38መኰንኖቹም ይህንኑ ቃል ለገዦቹ ነገሯቸው፤ እነርሱም ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲሰሙ ደነገጡ፤ 39እነርሱ ራሳቸውም መጥተው ይቅርታ ጠይቀው ከወህኒ ቤቱ አወጧቸው፤ ከተማውንም ለቅቀው እንዲሄዱ ለመኗቸው። 40ጳውሎስና ሲላስ ከእስር ቤቱ ከወጡ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ሄዱ፤ በዚያም ወንድሞችን አግኝተው አበረታቷችው፤ ከዚያም በኋላ ሄዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ