መክብብ 10

10
1የሞቱ ዝንቦች ሽቱን እንደሚያገሙ፣
ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀልላል።
2የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ፣
የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራ ያዘነብላል።
3ሞኝ በጐዳና ሲሄድ ልበ ቢስ ነው፤
ጅል መሆኑንም ለማንም ይገልጻል።
4የገዥ ቍጣ በተነሣብህ ጊዜ፣
ስፍራህን አትልቀቅ፤
ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋልና።
5ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤
ይህም ከገዥ የሚወጣ ስሕተት ነው፤
6ሞኞች በብዙ የክብር ስፍራዎች ሲቀመጡ፣
ሀብታሞች ግን በዝቅተኛ ስፍራ ሆነዋል።
7መሳፍንት እንደ ባሮች በእግራቸው ሲሄዱ፣
ባሮች ፈረስ ላይ ተቀምጠው አይቻለሁ።
8ጕድጓድን የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤
ቅጥርንም የሚያፈርስ እባብ ይነድፈዋል።
9ድንጋይ የሚፈነቅል ይጐዳበታል፤
ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።
10መጥረቢያ ቢደንዝ፣
ጫፉም ባይሳል፣
ብዙ ጕልበት ይጨርሳል፤
ብልኀት ግን ለውጤት ያበቃል።
11እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣
ለደጋሚው ምንም አይጠቅመውም።
12ከጠቢብ አፍ የሚወጣ ቃል ባለሞገስ ነው፤
ሞኝ ግን በገዛ ከንፈሩ ይጠፋል፤
13ቃሉ በመጀመሪያ ሞኝነት ነው፤
በመጨረሻም ደግሞ ክፉ እብደት ነው፤
14ሞኙም ቃልን ያበዛል።
የሚመጣውን የሚያውቅ ሰው የለም፤
ከርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ሊነግረው ይችላል?
15የሞኝ ሥራ ራሱን ያደክመዋል፤
ወደ ከተማ የሚወስደውንም መንገድ አያውቅም።
16አንቺ፣ ንጉሥሽ ልጅ#10፥16 ወይም አሽከር የሆነ፣
መሳፍንትሽም በጧት ግብዣ የሚያደርጉ ምድር ሆይ፤ ወዮልሽ!
17አንቺ ንጉሥሽ ከተከበረው ዘር የሆነ፣
ለመስከር ሳይሆን ለብርታት፣
በተገቢው ጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ ምድር ሆይ፤ ብፁዕ ነሽ።
18ሰው ሰነፍ ከሆነ ጣራው ይዘብጣል፤
እጆቹም ካልሠሩ ቤቱ ያፈስሳል።
19ግብዣ ለሣቅ ያዘጋጃል፤
ወይንም ሕይወትን ያስደስታል፤
ገንዘብም ካለ ሁሉ ነገር አለ።
20በሐሳብህም እንኳ ንጉሥን አትንቀፍ፤
በመኝታ ክፍልህም ባለጠጋን አትርገም፤
የሰማይ ወፍ ቃልህን ልትወስድ፣
የምትበረዋም ወፍ የምትለውን ልታደርስ ትችላለችና።

Currently Selected:

መክብብ 10: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ