ዘፀአት 22
22
ንብረትን ስለ መጠበቅ
1“አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ በአንድ በሬ ምትክ ዐምስት በሬዎች፤ በአንድ በግ ምትክ አራት በጎች ይክፈል።
2“አንድ ሌባ በር ሲሰብር ተይዞ ቢደበደብና ቢሞት፣ ተከላካዩ የደም ባለዕዳ አይሆንም፤ 3ነገር ግን ፀሓይ ከወጣች በኋላ ከተፈጸመ፣#22፥3 ወይም፣ ከመታው ሰውየው በነፍስ ግድያ ይጠየቃል።
“ሌባ የሰረቀውን መክፈል አለበት፤ ምንም ከሌለው ግን የሰረቀውን ይከፍል ዘንድ ይሸጥ። 4የሰረቀው እንስሳ በሬ ወይም አህያ ወይም በግ ከነሕይወቱ በእጁ ከተያዘ ዕጥፍ መክፈል አለበት።
5“አንድ ሰው ከብቶቹን በመስክ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ እንዲሁ ስድ ቢለቅቃቸውና የሌላውን ሰው መስክ ቢግጡ፣ ምርጥ ከሆነው ከራሱ መስክ ወይም የወይን ቦታ መክፈል አለበት።
6“እሳት ተነሥቶ ወደ ቍጥቋጦ ቢዘምትና ክምርን ወይም ያልታጨደን እህል ወይም አዝመራውን እንዳለ ቢበላ፣ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሳ ይክፈል።
7“አንድ ሰው ብሩ ወይም ንብረቱ ያለ ሥጋት ይጠበቅለት ዘንድ ለጎረቤቱ ሰጥቶ ሳለ ቢሰርቅበትና፣ ሌባው ቢያዝ ዕጥፍ ይክፈል፤ 8ሌባው ካልተያዘ ግን፣ የቤቱ ባለቤት በንብረቱ ስርቆት ላይ እጁ ይኑርበት ወይም አይኑርበት ይታወቅ ዘንድ ዳኞች ፊት#22፥8 በዚህም ሆነ በቍጥር 9 ላይ ያለው፣ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። 9አንድ ሰው በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ማንኛውንም ንብረት ያለ አግባብ በባለቤትነት ይዞ ሳለ፣ ‘የእኔ ነው’ ባይ ቢመጣና ክርክር ቢነሣ፣ ባለጕዳዮቹ ነገሩን ለዳኞች ያቅርቡት፤ ዳኞቹ ጥፋተኛ ነው ያሉትም#22፥9 ወይም፣ እግዚአብሔር ጥፋተኛ ነው ያለውም ለጎረቤቱ ዕጥፉን ይክፈል።
10“አንድ ሰው አህያ፣ በሬ፣ በግ ወይም ማንኛውንም እንስሳ በጎረቤቱ ዘንድ በዐደራ አስቀምጦ ሳለ እንስሳው ቢሞት ወይም ጕዳት ቢደርስበት ወይም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ፣ 11በሁለቱ መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሒ የሚያገኘው፣ ጎረቤቱ የሌላውን ሰው ንብረት እንዳልወሰደ በእግዚአብሔር ፊት በመማል ነው። ባለቤቱም ይህን መቀበል አለበት፤ የካሳም ክፍያ አይጠየቅም። 12እንስሳው ከጎረቤት ተሰርቆ ከሆነ ግን፣ ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። 13በዱር አራዊት ተበልቶ ከሆነ፣ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ፣ ስለ ተበላው እንስሳ ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም።
14“አንድ ሰው ከጎረቤቱ እንስሳ ተውሶ ሳለ፣ ባለቤቱ በሌለበት ቢጐዳ ወይም ቢሞት ካሳ መክፈል አለበት። 15ባለቤቱ ከእንስሳው ጋራ ከሆነ ግን፣ ተበዳሪው መክፈል የለበትም፤ እንስሳው ከተከራየም ለኪራይ የተከፈለው ገንዘብ ኪሳራውን ይሸፍናል።
ማኅበራዊ ኀላፊነት
16“አንድ ሰው ያልታጨችን ልጃገረድ አታልሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢያጐድል፣ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስት ያድርጋት። 17እርሷን ለርሱ የልጅቷ አባት በሚስትነት ለመስጠት ከቶ የማይፈቅድ ቢሆን፣ ለድንግሎች መከፈል የሚገባውን ማጫ አሁንም ቢሆን መክፈል ይገባዋል።
18“መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ።
19“ከእንስሳ ጋራ ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽም ሰው ይገደል።
20“ለእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አማልክት የሚሠዋ ይጥፋ#22፥20 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ፈጽሞ በማጥፋት ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያመለክት ነው።።
21“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና።
22“ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ። 23ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በርግጥ እሰማለሁ። 24ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የለሽ ይሆናሉ።
25“ከሕዝቤ መካከል ችግረኛ ለሆነው ለአንዱ ገንዘብ ብታበድሩ፣ እንደ ዐራጣ አበዳሪ አትሁኑ፤ ወለድ አትጠይቁት#22፥25 ወይም፣ ከልክ በላይ የሆነ ወለድ አትጠይቁ። 26የጎረቤትህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ሲመሽ መልስለት፤ 27ምክንያቱም ለሰውነቱ መሸፈኛ ያለው ልብስ ያ ብቻ ነው፤ ሌላ ምን ለብሶ ይተኛል? ወደ እኔ ሲጮኽ እኔ እሰማለሁ፤ እኔ ርኅሩኅ ነኝና።
28“በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል አታሰማ#22፥28 ወይም፣ ዳኞችን አትሳደብ፤ ወይም የሕዝብህን መሪ አትርገም።
29“የእህልህን ወይም የወይን ጠጅህን በኵራት ለእኔ ከማቅረብ ወደ ኋላ አትበል።
“የወንድ ልጆችህን በኵር ለእኔ ስጠኝ። 30ከቀንድ ከብትህና ከበጎችህም እንዲሁ አድርግ፤ ለሰባት ቀን ከእናቶቻቸው ጋራ ይቈዩ፤ በስምንተኛው ቀን ግን ለእኔ ሰጠኝ።
31“እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ የዘነጠለውን የእንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ለውሾች ስጡት።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.