ዘፀአት 24

24
ቃል ኪዳኑ ስለ መጽናቱ
1ከዚያም ሙሴን “አንተና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ ከሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ጋራ ወደ እግዚአብሔር ኑ፤ ከሩቅም ስገዱ አለው፤ 2ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችለው ሙሴ ብቻ ነው። ሌሎቹ መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከርሱ ጋራ መምጣት የለበትም።”
3ሙሴ ወደ ሕዝቡ ሄዶ የእግዚአብሔርን ቃሎችና ሕጎች ሁሉ በነገራቸው ጊዜ በአንድ ድምፅ ሆነው፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። 4ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ጻፈ።
በማግስቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ። 5ከዚያም ወጣት ወንድ እስራኤላውያንን ላከ፤ እነርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት#24፥5 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል። አቀረቡ፤ ወይፈኖችን የኅብረት መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ሠዉ። 6ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጐድጓዳ ሳሕኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው። 7ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ።
8ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባው የኪዳኑ ደም ይህ ነው” አላቸው።
9ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣ 10የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር#24፥10 ወይም፣ ላፒስ ላዘሊ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ወለል ነበር። 11ሆኖም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ አለቆች ላይ እጁን አላነሣባቸውም። እግዚአብሔርን አዩ፣ በሉ፤ ጠጡም።
12 እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በተራራው ላይ ወደ እኔ ና፤ በዚህም ቈይ፤ እኔም መመሪያ እንዲሆናቸው ሕግና ትእዛዞች የጻፍሁባቸውን የድንጋይ ጽላት እሰጥሃለሁ” አለው።
13ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋራ ዐብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። 14እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ ክርክር ያለው ባለጕዳይ ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው።
15ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤ 16እግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው። 17ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ክብር በተራራው ጫፍ ላይ እንደሚባላ እሳት ሆኖ ይታይ ነበር። 18ከዚያም ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ውስጥ ገባ፤ በተራራውም ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።

Currently Selected:

ዘፀአት 24: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ