ዘፀአት 25
25
ለመገናኛው ድንኳን የሚቀርቡ ስጦታዎች
25፥1-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥4-9
1 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2“ስጦታ እንዲያመጡልኝ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። ይሰጥ ዘንድ ልቡ ካነሣሣው ከእያንዳንዱ ሰው ስጦታን ተቀበልልኝ።
3“ከእነርሱ የምትቀበላቸው ስጦታዎች እነዚህ ናቸው፤
“ወርቅ፣ ብርና፣ ንሓስ፤
4ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና የበፍታ ድር ልብስ፣ የፍየል ጠጕር፤
5ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ፣ የለፋ ቈዳ፣ የግራር ዕንጨት፤
6ለመብራት የወይራ ዘይት፤
ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ መዐዛ ላለው ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞች፤
7በኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎች።
8“ከዚያም መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ፤ እኔም በመካከላቸው ዐድራለሁ። 9ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ልክ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት።
የቃል ኪዳኑ ታቦት
25፥10-20 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥1-9
10“ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት#25፥10 ርዝመቱ 1.1 ሜትር፣ ጐኑና ርዝመቱ 0.7 ሜትር ያህል ነው። እንዲሠሩ አድርግ። 11ውስጡንም ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት። 12አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል ሁለቱን በሌላ በኩል ከአራቱ እግሮች ጋራ አያይዝ። 13ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው። 14መሎጊያዎችንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ማእዘኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። 15መሎጊያዎቹ ከታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ምን ጊዜም መውጣት የለባቸውም። 16የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር።
17“ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል#25፥17 ርዝመቱ 1.1 ሜትር፣ ጐኑና ርዝመቱ 0.7 ሜትር ያህል ነው። የሆነ የስርየት መክደኛ#25፥17 በትውፊት፣ የጸጋው ዙፋን በመባል ይታወቃል። ከንጹሕ ወርቅ ሥራለት። 18በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ የሚሆኑ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል ሥራ። 19አንዱን ኪሩብ በአንደኛው፣ ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላኛው ዳር አድርግ በሁለቱም ጫፎች ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው ጋራ አንድ ወጥ አድርገህ ሥራቸው። 20ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት የስርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይሸፍኑ፤ እርስ በርሳቸው ትይዩ በመሆንም ፊታቸውን ወደ ስርየት መክደኛው ያድርጉ። 21የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ዐናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ። 22በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋራ እገናኛለሁ፤ ለእስራኤላውያን የሚሆኑትን ትእዛዞቼንም እሰጥሃለሁ።
የኅብስቱ ማስቀመጫ ጠረጴዛ
25፥23-29 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥10-16
23“ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሥራ።#25፥23 ርዝመቱ 0.9 ሜትር፣ ጐኑና 0.5 ርዝመቱ 0.7 ሜትር ያህል ነው 24በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። 25ዙሪያውንም አንድ ስንዝር#25፥25 ወደ 8 ሳንቲ ሜትር ያህል ነው። ስፋት ያለው ጠርዝ አብጅለት፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። 26ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ፣ አራቱ እግሮች ባሉበት በአራቱ ማእዘኖች ላይ አያይዘው። 27ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች ይይዙ ዘንድ፣ ቀለበቶቹ ከክፈፉ አጠገብ ይሁኑ። 28መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሥራቸው፤ በወርቅ ለብጣቸው፤ ጠረጴዛውንም ተሸከምባቸው። 29ለመጠጥ ቍርባን መፍሰሻ ይሆኑም ዘንድ ዝርግ ሳሕኖችንና ወጭቶችን፣ እንዲሁም ማንቈርቈሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖቹን ከንጹሕ ወርቅ ሥራቸው። 30በማንኛውም ጊዜ በፊቴ እንዲሆን በገጸ ኅብስቱ በዚህ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጥ።
የመብራቱ መቅረዝ
25፥31-39 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥17-24
31“ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ መቆሚያና ዘንግ አብጅለት፤ ጽዋ መሰል አበባዎች፣ እንቡጦችና የፈነዱ አበባዎች ከመቅረዙ ጋራ ወጥ ሆነው ይሠሩ። 32ከመቅረዙ ግራና ቀኝ ጐን ጋራ የተያያዙ፣ በአንዱ በኩል ሦስት በሌላው በኩል ሦስት በድምሩ ስድስት ቅርንጫፎች ይኑሩት። 33ከመቅረዙ ጋራ የተያያዙት ስድስቱ ቅርንጫፎች እያንዳንዳቸው እንቡጥና ቀንበጥ ያሏቸው የለውዝ አበባ ቅርጽ ያሏቸው ሦስት ጽዋ መሰል አበባዎች ጋራ ያኑሯቸው። 34በመቅረዙም ላይ አበባዎች እንቡጥና ቀንበጥ ያሏቸው አራት የለውዝ አበባ ቅርጽ ያሏቸው ጽዋዎች ይኑሩ። 35በመቅረዙ ላይ ላሉት ለስድስቱ ቅርንጫፎች እንቡጥ በመጀመሪያዎቹ ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር፣ ሁለተኛውም እንቡጥ በሁለተኛው ጥንድ ሥር፣ ሦስተኛውም እንቡጥ በሦስተኛው ጥንድ ሥር ይሁን። 36እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከመቅረዙ ጋራ አንድ ወጥ ሆነው ከንጹሕ ወርቅ ተቀርጸው ይሠሩ።
37“ከዚያም ሰባት መብራቶች ሠርተህ ከመቅረዙ ፊት ለፊት ለሚገኘው ስፍራ ብርሃን እንዲሰጡ ከመቅረዙ ላይ አስቀምጣቸው። 38መኰስተሪያና የኵስታሪ ማስቀመጫ ሳሕኖቹም ከንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 39ለመቅረዙና ለዕቃዎቹ ሁሉ የሚያስፈልገው አንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ነው። 40በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት መሥራትህን ልብ በል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.